2022-07-02 08:01:10
(ካህሊል ጂብራን)
በአፌ ውስጥ በስብሶ የሚያስቸግረኝ አንድ ጥርስ አለኝ በቀን ሰላማዊ ሆኖ ይውላል። ምሽቱ ሲገፋ፣ የጥርስ ሃኪሞቹ እንቅልፍ ሲጥላቸው እና መድሃኒት ቤቶቹ ሲዘጉ ግን ይጠዘጥዘኝ ይጀምራል።
አንድ እለት ትዕግስቴ ተሟጠጠና ወደ አንድ የጥርስ ሃኪም ሄጄ ያንን ስቃይ ያበዛብኝንና የምሽቴን ፀጥታ ወደ ማቃሰት እና ማጓራት በመለወጥ እንቅልፍ የነሳኝን ጥርስ እንዲነቅልልኝ ነገርኩት። የጥርስ ሃኪሙ ራሱን ከግራ ቀኝ እየወዘወዘ "ጥርሱን ማዳን ስንችል መንቀሉ ቂልነት ነው" አለኝ። ከዚያም ጎንና ጎኖቹን በስቶ ቀዳዳዎቹን በማፅዳት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሊመልሰው እና ከብስባሴው ሐራ ሊያወጣው ያለውን መንገድ ሁሉ ተጠቀመ። መብሳቱን ከጨረሰ በኋላ በንፁህ ወርቅ ሞላውና "የበሰበሰው ጥርስህ አሁን ከጤነኞቹ የበለጠ ጠንካራና ብርቱ ነው" አለኝ በኩራት። አመንኩት። ከፈልኩትና ስፍራውን ለቅቄ ሄድኩ።
ነገር ግን ገና ሳምንቱ ሳይገባደድ የተቀሰፈው ጥርስ ወደ ህመሙ ተመለሰና የነፍሴን ጥዑም ዜማ ወደ ለቅሶና ስቃይ ለወጠብኝ። እናም ወደ ሌላ የጥርስ ሃኪም አመራሁና "ምንም ጥያቄ ሳይጠይቀኝ ይህንን ጥርስ አውጥተህ ጣልልኝ። የደረሰበትና ያልደረሰበት ግልግልን እኩል አያውቃትም!" አልኩት።
ትዕዛዜን በማክበር ጥርሴን ነቀለልኝ። ከዚያም ጥርሴን እያየ "ይህ ጥርስ እንዲነቀል በማድረግህ መልካም አድርገሃል" አለ።
በአፍ ማህበረሰብ ውስጥ እስከ መንጋጋ አጥንት ድረስ የበሰበሱ ብዙ በሽተኛ ጥርሶች አሉ። ይሁንና ማህበረሰቡ እነዚህን የተበላሹ ጥርሶች ለማስነቀልና ከስቃዩ ለመገላገል ምንም ጥረት አያደርግም። ራሱንም በወርቅ ፍቅፋቂ ይሞላል። አብዛኞቹ የበሰበሱትን የማህበረሰብ ጥርሶች በሚያብለጨልጭ ወርቅ እንደሚያክሙ የጥርስ ሃኪሞች ናቸው ።
እንደዚህ ተጠጋግነው በመደለል የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ስቃይ ህመምና ሞት ዕጣ-ፈንታቸው ናቸው።
ሃገር አፍ ውስጥ ብዙ የበሰበሱ፣ ቆሻሻና ያመረቀዙ ጥርሶች አሉ። ሃኪሞቹ ከመንቀል ይልቅ በወርቅ ፍቅፋቂ አክመዋቸዋል። ህመሙ ግን እንዳለ ነው።
የበሰበሰ ጥርስ ያለው ሃገር የታመመ ጨጓራ እንደሚኖረው እርግጥ ነው። በዚህ ያለመፈጨት ችግር ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሃገራት አሉ።
ሃገር ዳቦውን በበሰበሰ ጥርሱ እንደሚያኝክ እና አንዳንዱም ጉርሻ ከተመረዘ ምራቅ ጋር በመዋሃድ በሽታውን በሃገሩ ጨጓራ ውስጥ እንደሚያሰራጭ ስትነግሯቸው "አዎ ግን የተሻሉ የጥርስ ሙሌቶች እና ማደንዘዣዎች እየፈለግን ነው" ይሏችኋል።
@millionsankara
655 views05:01