Get Mystery Box with random crypto!

ማሳሰቢያ፤ በአርቲስት መቅደስ ፀጋዬ! የኔ ታዋቂነትም ሆነ እንዳላችሁኝ የዕውቀት ደረጃ የአምላኬ | Michael Z Ethiop

ማሳሰቢያ፤ በአርቲስት መቅደስ ፀጋዬ!

የኔ ታዋቂነትም ሆነ እንዳላችሁኝ የዕውቀት ደረጃ የአምላኬን እናት በዐደባባይ እንዳላወድሳት የሚያደርገኝ ከሆነ #ጥንቅር_ብሎ_ይቅር! ቁርጥ መልሴ ነው።

ይህ የእኔ የግል ገጼ ሲሆን የኔን የግል አመለካከቶቼን እና እምነቶቼን የማንፀባርቅበት ነው። ሃይማኖቴ ደግሞ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሆኑ ይታወቃል። ኦርቶክሳዊነቴን እናትና አባቴ ስላወረሱኝ ብቻ ሳይሆን ዐውቄው፣ ተረድቼው ትክክለኛነቱን አምኜ አምላኬን የማመልክበት ሃይማኖቴ ነው።

ትናንት የለጠፍኩትን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ተከትሎ የመጡልኝን አንዳንድ የሌላ እምነት ተከታዮች አስተያየቶችን ንቄ ለመተው ብሞክርም በግል ስልኬ እየደወሉ ቅድስት ድንግል ማርያምን የማወድስበት መንገድ ከኔ እንደማይጠበቅ መንገር እና ስለ አምላኬ ለኔ ለመስበክ መሞከርን ግን #ከንቀት_ቆጥሬዋለሁ። እናም ይህ ሁኔታ ስለተደጋገመብኝ ነው አቋሜን ለመግለፅ ዐደባባይ መውጣት የፈለግኩት።

የኔ ታዋቂነትም ሆነ እንዳላችሁኝ የዕውቀት ደረጃ የአምላኬን እናት በዐደባባይ እንዳላወድሳት የሚያደርገኝ ከሆነ #ጥንቅር_ብሎ_ይቅር! ቁርጥ መልሴ ነው። እናቴን ገና መቼ አመሰገንኳትና! መቼ ገና አወደስኳት!.....በእኔ በኃጢያተኛዋ እና በደካማዋ ሴት የሷ ስም ሲጠራ ክብሩ ለኔ ነው! አምላኬ በምሕረቱ ባይጎበኝኝ፣ እመ አምላክ ባታማልደኝ የአምላኬ ማደሪያ የሆነችውን የእናቴን ስም የመጥራት ዐቅሙስ ባልኖረኝ ነበር! እና እስትንፋሴ እስካለች #ቅድስት_ድንግል_ማርያምን እናቴን አወድሳታለሁ! ስለ ማርያም አማላጅነት እመስክራለሁ!

እግዚአብሔር ይመስገን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሙሉ የአምላክነት ክብሩ አለ። ቤተክርስቲያን በቅዳሴዋ፣ በማህሌቷ በመዝሙሯ አምልኮ የምታደርገው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እናም የ80 ቀን ልጅ እያለሁ በጥምቀት የተቀበልኩትና የማውቀው የማመልከው አምላክ እያለኝ ጌታን ተቀበይ ብሎ ሙግት ለኔ አላዋቂነት ነው!

የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆናቹ እጅግ የምወዳችሁ እና የማከብራቸው ጓደኞቼ እንዲሁም ቤተሰቦቼ አብረን በቆየንባቸው ዓመታት አንድም ቀን ስለእምነት ልዩነት ሳታነሱ አብሮነታችን ፀንቶ እንዲቆይ ስላደረጋችሁ ሳላመሰግናቹ አላልፍም። ለናንተ ያለኝ ፍቅር ብቻ ነው ተባረኩልኝ

በስተመጨረሻም ሀገር በከፋ ችግር ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት እንደ ሕዝብ አንድነታችንን አጠናክረን በየእምነት ተቋማችን አምላካችን ለሀገራችን ምሕረቱን እንዲያመጣ እየከፋፈለን፣ እያጠፋን ካለው መንፈስ እንዲያላቅቀን መጸለይ እንጂ አንዱ የአንዱን ሃይማኖት በማንቋሸሽ ምዕመን ምልመላ ላይ መሯሯጥ አያዋጣንም።

ቸር እንሰንብት ወዳጆቼ!!