2022-08-06 07:59:14
ሱባዔና ሥርዓቱ
ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጾመ ፍልሰታን የሚጾሙበት ሱባዔ የሚገቡበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህ ወቅት ምእመናን ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ መልካም የሱባዔ ጊዜ ይሁንልን፡፡
ሱባዔ ምንድን ነው?
ሱባዔ በሰዋሰው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2፥2፤ መዝ.118፥64፡፡
ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ሱባዔ መቼ ተጀመረ?
ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ ሲል ቃልን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምንጦስ አንቀጽ አራት/፡፡
#ይቀጥላል ....
በቀጣይ ሱባዔ ምንድን ነው ጥቅሙ?
@menefesawimet
ሱባዔ ለምን?
#ክፍል_ሁለት
የሰው ልጅ፤ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፤ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡
በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡
ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡
እግዚአብሔርን ለመማፀን ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡
ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡
ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት ያድሯል፡፡ በነጋው ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ አለው፡፡እኔም እንዲሁ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡
ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡
ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡
ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡
#ይቀጥላል
በቀጣይ ክፍል ሱባዔ ለመግባት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት?
@menefesawinet
ሱባኤ ለመግባት መደረግ ያለበት ዝግጅት
ክፍል ሦስት
ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት ኣስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት ኣስፈላጊ ነው፡፡
ቅድመ ዝግጅት
ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/ በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ኣንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት ኣለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሓ ኣባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በኣባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ ኣባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ኣንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሓ ኣባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡
882 viewsĎň_ťėŕėfê_ŧëšfãýê @webzema, edited 04:59