Get Mystery Box with random crypto!

ሊቁ አባ ሕርያቆስ +'+ =>ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋ | መዓዛ ሃይማኖት የበጎ አድራጎትና ጉዞ ማህበር

ሊቁ አባ ሕርያቆስ +"+

=>ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል:: አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል:: ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት::

+አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ብየ ትክክለኛውን ዓ/ም ለመናገር ይከብደኛል:: ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን 4ኛው: ወይ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል::
+ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው:: ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን: የዋህና ገራገር ነበረ:: መቼም እመቤታችን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን:: ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ: ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ::
+የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር:: ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም:: የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ::
+ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምሕርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው:: ከትምሕርት ወገንም የሰሞን ጉዋዞችን: አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር::
+በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ: መላልሶ ያመሰግንበት ነበር:: ከዳዊት መካከል ደግሞ መዝ. 44ን ፈጽሞ ይወዳት ነበር:: ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው:: የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው::

+አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ: ቁሞም ተቀምጦም: ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቁዋረጥ ይላት ነበር:: እየጣፈጠችው "ልቡናየ በጐ ነገርን አወጣ" እያለ ይዘምር ነበር:: በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤዺስ ቆዾስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ::
+ምንም አለመማሩ ቢያሰጋችቸውም "በጸሎቱ: በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል" ብለው ሾሙት:: ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት: ይንቁትም ነበር:: እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው: እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር::

+አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል:: በበርሃ ብቻውን እየተራመደ: "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ: ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ:: እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር:: ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ::

+በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው:: ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም:: ልብሱም አልቆሸሸም:: ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር::
+"እመ ብርሃን!" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው:: እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ::
+የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር:: እመቤታችን አነጋገረችው: ባረከችው:: ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ: ምግብም ሳይበላ: እዚያው ገደሉ ውስጥ ለ1 ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል::
+በሁዋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሐገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በሁዋላም አንድ ፈተና ገጠመው:: አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት 1 ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን" አሉ::
+እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም: እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ" አላቸው:: "አይሆንም" ብለው እርሱኑ አስገቡት:: ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር:: ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው" አሉት::

+ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው:: እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት:: አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ:: ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን: መገፋቴን ተመልከች" አላት::
+ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው):: በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው:: ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል 2ቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ:: እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው::

+ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ: አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ" አሉ:: ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት:: እሳት ሳያቃጥለው: ውሃ ሳይደመስሰው ቀረ::
+መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል:: ከዚህች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር 1 ሊቅ ሆነ:: ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (10,000) ናቸው:: ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል:: ይህቺ ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት::
ከቅዱሱ ረድኤት በረከት ያካፍለን በጸሎቱ ይማረን