2022-06-14 18:33:57
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †††
ሰኔ ፯
ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
➢ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው፣ በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው።
➢ ሊቁ የተወለደው መጋቢት ፳፯ ቀን በ፬፻፴፫ ዓ.ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው። ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር።
➢ አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በሦስት ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው። ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕፃኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ። ሊቀ ጳጳሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው። የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምሥጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ ሦስት ነገሮች ያስፈሩኛል።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።
ጳጳሱና ሕዝቡ ወደ ሕፃኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት።
#እርሱም፦
፩.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
፪.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
፫.ከፈጣሪዬ የፍርድ ቃል ሲወጣ አላቸው።
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ጳጳሳቱ "እግዚአብሔር በዚህ ሕፃን አድሮ ዘለፈን።" እያሉ ለንስሐ በቅተዋል።
➢ ቅዱስ ያዕቆብ ሰባት ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት። በአምስት ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ሊቅ ሆኗል። በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ እርሱ ተሰብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን። አዲስ ምሥጢር ንገረን?" አሉት። እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው።
➢ "እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን?" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል። ፈጣሪንም አመስግነዋል።
# ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን፣ ዕጸበ ገዳምን፣ ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል። በድንግልናው ጸንቶ ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል። በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት።) ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል።
#በዘመኑም፦
፩.የ፬፻፶፩ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል።
፪.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል።
፫.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል።
፬.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል።
➢ በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በሰባ ሁለት ዓመቱ በ፭፻፭ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ ፳፯ ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ። ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች።
➢ ሰኔ ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
፪.ቅዱስ፣ ቡሩክና አሸናፊ አባ አበስኪሮን (ታላቅ ሰማዕትና ባለ ብዙ ተአምራት)
፫.አሥራ ስድስት ሺህ ሰማዕታት (በአንድ ቀን የተገደሉ)
፬.የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተከፈተበት በዓል (ከአንድ ሺ ዓመታት በፊት ምስር (CAIRO) ውስጥ)
➢ ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
"ይህንን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው። እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ።"
፩ጢሞ ፬፥፲፩-፲፫
✥••┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈••✥
አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን።
✞✞✞✞✞ አሜን ✞ች✞✞✞✞
✥••┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈••✥
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዴቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
✞✞✞✞✞
✞✞✞ ሃሳብ ➢
@gebrye_comment_bot
|❀:✧๑ ✞✞✞✞✞✞✞ ๑✧❀|:
✞✞✞ ይቀላቀሉ ➣
@mahteben_albetsm
111 viewsማህተቤን አልበጥስም, 15:33