Get Mystery Box with random crypto!

“የቀዶ ጥገናው ክፍል AC ክፍሉን ለማቀዝቀዝ ይሞክራል። ከፍተኛ የሆነ ፀጥታ በክፍሉ ውስጥ ቢኖርም | ማዕዶት የመጽሀፍት መደብር Maedot Books Store

“የቀዶ ጥገናው ክፍል AC ክፍሉን ለማቀዝቀዝ ይሞክራል። ከፍተኛ የሆነ ፀጥታ በክፍሉ ውስጥ ቢኖርም ለስለስ ያለ የአስቴር ዘፈን በቀስታ ይንቆረቆር ነበር። ብዙ አስቸጋሪ ብለን የለየናቸው የቀዶ ጥገናው ክፍሎች(steps) ቀስ በቀስ ያልፉ ጀመር።

እነሆ በከፍተኛ መመሰጥ ሆነን ስድስት ሰዓታት አለፉ። ሁሉም ነገር በሠላም የሠራን መሰለን። መደሰት ግን አልጀመርንም። ምክንያቱ ደግሞ ሁልጊዜ የዚህ ዓይነቱ ቀዶ ጥገና Bental Procedure ችግሩ ኦፕሬሽኑ ካለቀ በኋላ ደም
መፍሰስን ማቆም የሁልጊዜ ፈተና ስለሆነ ነበር። እናም አለም በደረሰበት የወቅቱ ደረጃ ሁሉንም ጨርሰን እንደተለመደው ከአንድ አስቸጋሪ ቦታ ላይ
በብዛት ደም ሲፈስ ማየት ጀመርን። የፈራነው ደረሰ። ላለመረበሽ እየሞከርን የተቻለንን ያህል ተረጋግተን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጋችንን ቀጠልን። ይሁን እንጂ አልተሳካልንም ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ከቦታው የሚፈሰው ደም ከመጨመሩም ባሻገር ይህ ቦታ የቀኝ የልብ የደም ስር ካስገባነው ሰው ሰራሽ የደም ቧንቧ (Artificial Aortic conduit) የሚነሳበት ስለነበር ነው።
በየደቂቃው ልብ ይበልጥ ይጎዳ ጀመር፡፡ አሁን በሁላችንም ላይ መደናገጥ መታየት ጀመረ። ምንም እንኳን ልብና ሳምባን ከማሽን በሰላም አላቀን ወደ ተፈጥሮው ተመልሰን የነበረ ቢሆንም ሁሌም እንደሚደረገው ደም ማፍሰስን
ለማቆም የሚሰራውን ከዚህ በኋላ ልብ እየመታ መሆኑ ነው።
ይሄንን አስቸጋሪ ሁኔታ መቆጣጠር ተሳነን። እናም ቀዶ ጥገናውን ከጀመርን ከ7:00 ሰዓት በኋላ በጠቅላላው ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዝን
አስተዋልኩኝ። መሯሯጥ በዛ፤ እናም የዚህን ወጣት ነብስ ለማዳን አንድ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ቡድኑን አረጋግቼ እቅዴን አንድ በአንድ አስረዳሁ። እናም እንደገና ተመልሰን ልብና ሳንባን አቆምን፡፡ የደም ዝውውርን ለማሽን በድጋሚ ሰጠን፤ እናም አደገኛ ድካም ተሠምቶኝ ስለነበር በዚህች ወሳኝ ሰዓት ራሴን እንዳልስት ብዬ እረፍት ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ልብሴን አወለቅኩ። ከጭንቅላቴ ላይ ሁሉንም መሳርያ አወለቅሁ። ፊቴን ታጥቤ አንድ ብርጭቆ ትኩስ ሻይ ጠጣሁ።

ጥቂት ደቂቃ ካረፍኩ በኋላ ተመልሼ ታጠብኩ፡፡ እንደገና የቀዶ ጥገና ልብሴን ለብሼና መሳሪያዎችን በሙሉ በዓይኔና በጭንቅላተረ ላይ አድርጌ ገባሁ።
እንደገና ልብን ሙሉ ለሙሉ በድን በማድረግ (On Cross Clamp) የሚደማውን ቦታ በእርጋታ መለየት ጀመርን። ቀጥሎ ቀስ በቀስ የቀኝ የደም
ቧንቧን ሳንጎዳ ችግሩን ለመፍታት ሞከርን። ጥሩ ስሜት ተሰማን፡፡

አሁንም ቢሆን ግን ቦታው አለመድማቱን ማረጋገጥ የሚቻለው ልብ መምታት
ሲጀምርና ከማሽን ስናላቅቅ ብቻ ነው። ሁላችንም በልባችን እየፀለይን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሮቶኮሉ መሠረት ልብና ሳንባን ከማሽን አላቀቅን ቦታውን
በጥንቃቄ መመርመር ተያያዝን። የድል ብስራት ስሜት ወረረኝ። ልብ ተመችቶት ይመታል፤ ሳንባም በጥሩ ሁኔታ ኦክስጅን ያቀብላል፤ የምናያቸው መስፈርቶች በሙሉ ፅድት ያሉና የእኛን ልብ በደስታ የሚሞሉ ነበሩ። እነሆ ቢላችንን
ካሳረፍን ከ10:00 ሰዓት በኋላ የወጣቱ ደረት ተዘጋ። ሀሉም ነገር ደስ ይል
ነበር።

ጥሩ እንቅልፍ ተኛሁ መሰል ጠዋት ትኩስነት ተሰማኝ። ቀጣዩ ቀን እሁድ ነበርና በባዶው የቦሌ መንገድ በርሬ ወደ ሆስፒታል ሄድኩኝ። ምንም እንኳን ሌሊቱን አለመደወሉ የሚነግረኝ ጥሩ ምልክት ቢኖርም በአካል ሄጄ ይህን የ27 ዓመት
ወጣት እስካየሁ ጓጓሁ፤ በቦታው ስደርስ ከማሽን ventilator ተላቋል፤ በራሱ ይተነፍሳል፤ ምንም ደም አልፈሰሰውም። ደስ አለኝ። ነገር ግን አዕምሮው ሙሉ በሙሉ ጥርት አላለም ነበር፡፡

በዚያኑ ቀን ሁለት ሦስቴ እየተመላለስኩኝ አየሁት። ሰኞ ጠዋት እንደዚሁ በጉጉት መጥቼ ሳየው ደስ የሚል ፈገግታ እያሳየኝ እንዲህ ሲል ጠየቀኝ "
ሠራኽው አይደል" አለኝ እኔም አዎን ሁሉም መልካም ነው አልኩት "ጀግናዬ ነህ" አለኝ፡፡

እናም ሁለት ቀን ሙሉ ያጣሁትን ደስታ አሁን ግልብጥ ብሎ መጣ። የደስታ ጎርፍ አጥለቀለቀኝ ሁሉም ነገር አበቃ። አይደለም አንድ አስር ሞት መጥቶ ቢወስደኝ እኔ ጣጣ አለኝ?ቀዶ ጥገናውን በሰራን በዓመቱ ከሚኖርባት የገጠር ከተማ በጓሮው ያበቀለውን ሽንኩርት በማዳበርያ ጭኖ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ አበረከተልኝ።”

የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ:_ በ ዶ/ር ፈቀደ አግዋር


ከመፅሐፉ ትንሽ ለቅምሻ
መልካም የንባብ ጊዜ