Get Mystery Box with random crypto!

ባዶ ቦታ የሚታይ ነገር አለ...? የሚዳሰስስ...? እንቅ አድርጎ ይዞ አንገቱን ጨምድዶ | 💌💌💌💌MESSAGE 💌💌💌💌

ባዶ ቦታ

የሚታይ ነገር አለ...? የሚዳሰስስ...? እንቅ አድርጎ ይዞ አንገቱን ጨምድዶ ወይንም ደግሞ... እንዳይጋረፍ ፣ እንዳይጎዳን ፣ እንዳያስጨንቀን ፣....ጠቅልለን የሆነበት እንድናስቀምጠው ... ይታዘዘናል...?

ዝናብ ሲመጣ ሰው ሲሯሯጥ... ፀሀይ ስትበረታ ጥላ ጥላ ሲሸሸጉ... ጨለማ ሲመጣ ብርሃን ሲፈልጉ ... ቀልድ ይሁን ሙሾ ሳያውቁት ወይንም ሳላውቀው ሲያላዝኑ.......... ለእኔ ምኑም አይገባኝም። የማስበው.... ትናንት የነበርኩበት ቦታ ዛሬም እንዳለሁበት ይሰማኛል። ነገሮች ሁሉ ሲለዋወጡ... ለእኔ እንደነበሩ ናቸው።
አይቀዘቅዙ ፣ አያቃጥሉ ፣ አይጨልሙ ፣ አይገርሙ...አይደንቁ። ብቻ ...አላውቅም። በነጠብጣብ ባዶ ቦታ ለቅቄ ...ሰው የመሰለውን ይክተት(...........)

የድሮ አስተሳሰብ ናፍቋችሁ አያውቅም...? እንደውም ላስታውሳችሁ... የሰማይ መጨረሻ ከፊት ለፊትታችን ያለው ተራራ እንደሆነ (የዓለም ጠበብት መጡና 'ሰፊ ናችሁ' ብለው ሳይበታትኑን በፊት) የምናውቅ ፣ ሽንት ስንሸና... በክንዳችን ልክ ለክተን የምንቀመጠው ነገር (የእናታችን ጡት...) ... በእንደዚህ አይነት ስሜት ያለሁ ይመስለኛል።

ስታኮርፊ ኩርፊያሽ ... ዓለምን ያናውጠዋል(የእኔን) ። ስትቆጪ...ህይወት ከንቱ ትሆናለች(የእኔ)። ልትለዪኝ ስታስቢ... ምድርና ሰማይ ሲጋጩ... እኔ ተመልካች ሆኜ... እያንዳንዱን የሰውነቴ ክፍል ሲጨፈላለቅ ይታየኛል።
በመጨፈላለቅም ውስጥ ሆኜ ... በማይታዩ ...በማይዳሰሱ ...ይህ በማይባሉ ጥቃቅን ትዝታዎች ታጅቤ ወደቀድሞው ፍቅራችን እመለሳለሁ። ያው የድሃ ሃብቱ እንቅልፉም አይደል... ፍቅሩን ያጣ ሰው ታድያ ድሃ አይደል... ታድያ እንቅልፍ ከትዝታ በምን ይለያሉ...? አይዳሰሱ ፣ አይጨበጡ...እንደውም አገልግሉታቸውም ይመሳሰላል። ድሃ በእንቅልፉም አይደል ቅቤ የሚጠጣው..? አፍቃሪስ( ያጣ አፍቃሪ) ፍቅሩን የሚያገኘው ከትዝታው አይደል..?

ተውኝ..............መሮኛል(ባዶ ቦታውን ሙሉት!)



በንጉሡ ተሰማ(ጢያ)

@yenagtm
@yenagtm