Get Mystery Box with random crypto!

#ምክር_ለወዳጅ ይህን ፅሁፍ ማንበብ 100 መፅሐፍት የማንበብ ያህል ነው። በወጣትነት ሁሉም | Love ብቻ

#ምክር_ለወዳጅ

ይህን ፅሁፍ ማንበብ 100 መፅሐፍት የማንበብ ያህል ነው።

በወጣትነት ሁሉም ነገር ትክክል ነው ከሚል መመሪያ ውጣ፤ ሁሉንም ካላየሁ አላምንም አትበል። ሰምቶ ማመን፣ ከተጎዱት መማር አስተዋይነት መሆኑን አትርሳ። የሰማንያ ዓመት ዕውቀትን ለመገብየት ግድ ሰማንያ ዓመት መኖር የለብህም። ሰማንያ ዓመት ከኖሩት በትሕትና መጠየቅ ይገባሃል።

ምክርን ብትሰማ በነጻ ትማራለህ። ምክርን አልሰማ ብትል ግን በዋጋ እንደምትማር እወቀው! በዋጋ መማር ግን አድካሚ ደግሞም የሚያስመርር ነው። ብልህ ከሆንክ በሰው ከደረሰው ትማራለህ፤ ሞኝ ከሆንህ ግን በራስህ ሲደርስ ትማራለህ።

የታየህን አሳይ፣ ያልታየህን አጥራው። በደንብ ያልተረዳኸውን አታስተምረው። ያልቀመስከውን ለሰው አትጋብዝ። የሰማኸውን ሁሉ አትመን። ያየኸውን ሁሉ ስጡኝ፣ የተናገርከውን ሁሉ ፈፅሙ አትበል። የሰጠኽውን እርሳ እንጂ አታውራ። ፍፃሜውን ሳታይ ምስጋና አታብዛ። ቀኑ
ሳይመሽ ቀኑ ጥሩ ነው አትበል።

ዓይንህ የፊቱን ቢያይ፤ ልብህ የኋላውን ያስብ። ነገ ላይ እንድትደርስ፤ የትናንቱን አትርሳ። የምትሄድበት እናዳይጠፋህ የመጣህበትን አትዘንጋ።

የአባቶችህን መልካም ሥራ አብነት አድርግ። ካሳለፉት ሕይወት ተማር እንጂ አወዳሽና ወቃሽ አትሁን። ሌሎች መሆን ያለባቸውን ስታውቅ አንተ መሆን ያለብህ እንዳይጠፋህ ተጠንቀቅ። ደግሞም አንተም በታሪክ ፊት መሆንህን እወቀው።

ክፋት አይሙቅህ፣ መልካም ነገርም ብርድ ብርድ አይበልህ። ለክፋት አቅም ካለህ ለበጎ ነገርም አቅም አለህና ተግባርህ የምርጫ ውጤት ነውና አስብበት።

ገንዘብ የሚመልሰው የገንዘብን ጥያቄ ብቻ ነውና ሁሉንም ነገር ገንዘብ ያስገኝልኛል ብለህ አታስብ። ላለው አትሩጥ፣ ምጽዋትህና ተግባርህ በአቅምህ መጠን ይሁን እንጂ ከአቅምህ አትነስ። ድሃም ሆነህ ተበድረህ ስጦታ አትስጥ። በጣም ካልቸገረህ ለቅንጦት አትበደር። ያንተን ድርሻ ከጨረስህ ያልተጨረሰ የሌሎችን ድርሻ ፈፅምላቸው።

ለሀብታም አትሳቅ፣ የደሀ ጉልበት አይለፍብህ፣ ያለ ሰው ሰው አልሆንክምና ሰው አትጥላ፣ የወጣህበትን መሰላል አትገፍትር፣ ለመውረድም ያስፈልግሃልና፣ ያየኽውን ሴት ሁሉ የመውደድ ጠባይህ ካለቀቀህ ትዳር አትያዝ፣ ካልጋበዙህ በቀር አማካሪ አትሁን፣ ባልጠሩህ ሥፍራ አቤት አትበል፣ ካልሾሙህ መሪ አትሁን፣ ጉድለት በሌለበት ቦታ ጊዜህን አታባክን፣ የሰው ፊት ጥገኛ ሁነህ ሲስቁልህ የምትስቅ ሲቆጡህ የምታለቅስ አትሁን፣ ነገርህን በልክ፣ ቃልህን በጣዕም፣ ድምፅህን በዝግታ ፈፅመው።

እውር እንዳይሉህ ያልታየኽን አያለሁ አትበል። ጨካኝ እንዳይሉህ ያልተሰማህን ጩኸት እሰማለሁ አትበል። ንፉግ እንዳይሉህ ያለ አቅምህ እረዳለሁ አትበል። ነገር አይገባውም እንዳይሉህ ያልገባህን እንደገባህ አድርገህ አትለፍ። አንድ በጎ ዕውቀት ሳትጨብጥ የዋልክበትን ቀን እንደ ኖርክበት አትቁጠረው፣ ስለዚህ መፅሐፍትን አንብብ፣ አዋቂዎችን ጠይቅ፣ ሁሉን ሳትንቅ ስማ።

ሥልጣን ሲሰጥህ መሪ እንጂ አለቃ አትሁን፤ ከፊት እየቀደምህ አስከትል እንጂ ከኋላ ሆነህ አትቅደም።

በዓላማ ኑር፤ እንቅፋቶች የሚያጸኑህ እንጂ ተግባርህን የሚያስተውህ አይሁኑ። ሕይወት ትምህርት ቤት መሆኑና ባለማወቅ ብዙ ትህምርቶች እንዳያመልጡህ ተጠንቀቅ።

የመከራ ቀን ወዳጆችህን አትርሳ፤ የዛሬ ሰው ብቻ አትሁን።

ምንጩን ያላወቅነው ከማህበራዊ ሚዲያ የተወሰደ

@love_nw19