Get Mystery Box with random crypto!

በ ዲናዊ ጉዳይ ላይ አለመግባባት ሲኖር ~ 1- በቅድሚያ አላህን እንፍራ። በጉዳዩ ላይ በሚኖረን ድ | Bilal Media & Communication

በ ዲናዊ ጉዳይ ላይ አለመግባባት ሲኖር
~
1- በቅድሚያ አላህን እንፍራ። በጉዳዩ ላይ በሚኖረን ድርሻና ተሳትፎ መጠን አላህ ፊት መጥጠየቅ እንዳለ ከልብ እናስብ። ይህንን ማሰባችን በጉዳዩ ላይ ድንበር እንዳናንልፍ ያግዘናል።

2- "ተሳስቷል" ብለን ያሰብነው አካል የእውነት ተሳሳቷል ወይ የሚለውን ከስሜትና ግለት ነፃ ሆነን እንመርምር። ከመረጃ አንፃር፣ ከዑለማእ አካሄድ አንፃር፣ ካለንበት ቦታና ጊዜ ተጨባጭ አንፃር ፣ አስገዳጅ ሁኔታዎች ወይም ሚዛን የሚደፉ ስጋቶች ካሉም ታሳቢ በማድረግ ረጋ ብለን እንፈትሽ። ስህተት የመሰሉን ነገሮች ስህተት ላይሆኑ፣ ወይም ስህተት እንኳ ቢሆኑ ቀድመን በገመትነው መጠን የሚደርሱ ላይሆኑ ይችላሉ።

3- ስህተት እንዳለ እርግጠኛ ከሆንንም ስህተቱ የዐቂዳ ወይም የመንሃጅ ነው? ወይስ እዚያ አይደርስም? የሚለውን ከጥላቻና ስሜታዊነት ወጥተን እንመልከት። በራሳችን ከመደምደማችን በፊት መሰል ስህተቶችን ዑለማዎች በምን መልኩ እንደሚይዟቸው እናጣራ። ይህንን መለየታችን በደለኛ ብይን ሰጥተን ሰው እንዳንበድል፣ ራሳችንንም እንዳንጎዳ፣ ደዕዋ እንዳንበጠብጥ ይጠቅመናል። በኢጅቲሃዳዊ ርእሶች ጭምር ድንበር የሚያልፉ ሰዎች እንዳሉ ማወቅ መሰል ጥፋት ላይ እንዳንወድቅ ሊያነቃን ይገባል።

4- አንድ ስህተት የመንሃጅ ስህተት መሆኑ #ብቻውን የተሳሳተን አካል ሁሉ በቢድዐ ለመፈረጅ ሁሌ በቂ መነሻ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ :-
- ለተብዲዕ ከመቸኮላችን በፊት "ሰውየው ዑዝር አለው ወይ?" ወይም በቢድዐ እንዳንፈርጅ የሚገታን ነገር አለ ወይ? የሚለውን እንለይ። ከነ ጭራሹ ይህንን የማያውቁ ሰዎች አላህን ፈርተው ዝም ቢሉ ትርፉ ከምንም በላይ ለራሳቸው ነው።
- "አጥፍቷል" የምንለውን አካል ንግግሩን በትክክል እንረዳ። አንዳንዱ በጥላቻ ስለተሞላ በራሱ መንገድ ተርጉሞ ነው ምላሽ የሚሰጠው። ጩኸት እንዳይሸውደን።
- "አጥፍቷል" የምንለውን አካል ሙሉ ንግግሩን አግኝተናል ወይስ የቀረ ነገር አለ? እርግጠኛ እንሁን። ነገ አላህ ፊት መቆም እንዳለ አንርሳ። በጥላቻ ወይም በቡድንተኝነት ተገፋፍተን የሌሎችን ንግግር ቀጣጥለን፣ አጋነን፤ አዛብተን፣ ... ብናጠለሽ ዛሬ ሰዎችን ብንሸውድ አላህን የምንሸውድ እንዳይመስለን። ለራሳችን ስንል እንወቅበት።

5- ደግሞም የአካባቢያችንን ተጨባጭ እናስተውል። የሱና እንቅስቃሴ ደካማ በሆነበት አካባቢ ውስጥ እየኖሩ ያለችውን ትንሽ ጭላንጭል በሚያዳፍን ወይም በሚያቀጭጭ መልኩ ያለ ጥንቃቄ ልዩነትን ማራገብ ሞኝነት ነው። ይበልጥ የከፉ ለሆኑ አንጃዎችም ድጋፍ መስጠት ነው የሚሆነው። ስለዚህ መተራረማችን ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል።

በተረፈ ከነፈሰው ጋር ሁሉ የምንነፍስ፣ የጮኸ ሁሉ የሚወስደን የዋሆች አንሁን። በቅጡ በማናውቀው ጉዳይ ውስጥ በጭፍን ሰው ተከትለን አንግባ። በባህሪያቸው ረብሻ የሚመቻቸው፣ ዝምታ የሚያስጨንቃቸው አካላት ያጋጥማሉ። የነሱ ጩኸት ሰለባ እንዳንሆን እንጠንቀቅ።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor