Get Mystery Box with random crypto!

#ነነዌ_እና_የአጽዋማትና_በዓላት_አወጣጥ ❖ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዐት | መሠረተ ግእዝ

#ነነዌ_እና_የአጽዋማትና_በዓላት_አወጣጥ

❖ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዐት መግቢያቸውና መውጪያቸው የሚዘዋወር የሐዲስ ኪዳን አጽዋማትና በዓላት 11 ናቸው፡፡ እነዚህም ጾመ ነነዌ ፣ በአተ ጾም(ዐቢይ ጾም) ፣ ደብረ ዘይት ፣ ሆሣዕና ፣ ስቅለት ፣ ትንሣኤ ፣ ርክበ ካህናት ፣ ዕርገት ፣ ጰራቅሊጦስ ፣ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት ናቸው፡፡ ሁሉም የሚገቡበትን ለማወቅ መሠረታቸው ነነዌ ነው፡፡

→ ዐቢይ ጾም ነነዌ በገባ በ14ኛው ቀን ይገባል፤
→ ደብረ ዘይት ነነዌ በገባ በ41ኛው ቀን ይውላል፤
→ ሆሣዕና ነነዌ በገባ በ62ኛው ቀን ይውላል፤
→ ስቅለት ነነዌ በገባ በ67ኛው ቀን ይውላል፤
→ ትንሣኤ ነነዌ በገባ በ69ኛው ቀን ይውላል፤
→ ርክበ ካህናት ነነዌ በገባ በ93ኛው ቀን ይውላል፤
→ ዕርገት ነነዌ በገባ በ108ኛው ቀን ይውላል፤
→ በዓለ ኀምሳ ነነዌ በገባ በ118ኛው ቀን ይውላል፤
→ ጾመ ሐዋርያት ነነዌ በገባ በበ119ኛው ቀን ይገባል፤
→ ጾመ ድኅነት ነነዌ በገባ በ121ኛው ቀን ይገባል፡፡
ስለዚህ አንድ ጊዜ የነነዌ መግቢያ ከታወቀ ሌሎቹን ማግኘት ቀላል ነው፡፡

❖ ነነዌን ለማግኘት ደግሞ ጥልቅ ከሆነው የባሕረ ሐሳብ ትምህርት በጥቂቱም ቢሆን ማወቅ ግድ ነው፡፡ ከብዙ መንገዶች ውስጥ አንዱን ብቻ እናያለን፡፡

❖ ነነዌን ለማግኘት ዓመተ ዓለም፣ መጥቅዕ፣ ወንበር፣ መደብ፣ የዕለታት ተውሳክ፣ መባጃ ሐመር፣ ዐቢይ ቀመር፣ ማእከላዊ ቀመር፣ ንኡስ ቀመር የተባሉትን የስሌት ጽንሰ ሐሳቦችን መረዳት ተገቢ ነውና በቅድሚያ እነርሱን እያብራራን እናስላ፡፡

✥ ዓመተ ዓለም፦
የዘመነ ብሉይና የዘመነ ሐዲስ ድምር ነው፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው ዓመተ ዓለም 5500 + 2014 = 7514 ይሆናል፤

✥ ዐቢይ ቀመር፦
በባሕረ ሐሳብ ትምህርት በየ502 ዓመቱ የሚመጣውን ዑደት (ሳይክል) ዐቢይ ቀመር እንለዋለን፡፡ (ወንጌላውያን በየዐራት ዓመቱ የሚመጡ መሆናቸውን ዐውደ ወንጌላውያን በሚለው ቃል፣ ዓመት የ365/6 ቀናት ዑደት መሆኑን ዐውደ ዓመት በሚለው ቃል፣ ወር የ30 ቀናት ዑደት መሆኑን ዐውደ ወርኅ በሚለው ቃል፣ ሳምንት የ7 ቀናት ዑደት መሆኑን ዐውደ ሳምንት በሚለው ቃል እንደምንገልፀው በየ502 ዓመቱ የሚከሰቱ ክስተቶችን በዐውደ ቀመር እንጠራቸዋለን፡፡ ቁጥሩንም ዐቢይ ቀመር እንለዋለን፡፡) ብዙ ማብራሪያ ያለው ቢሆንም ለጊዜው ዐቢይ ቀመር 502 ዓመት መሆኑን መያዝ በቂ ነው፤

✥ ማእከላዊ ቀመር፦ ይህ 76 ዓመት ነው፤

✥ ንኡስ ቀመር፦ ይህ 19 ዓመት ነው፤

✥ መደብ፦ ማለት ዓመተ ዓለም ለዐቢይ ቀመር ተካፍሎ፣ ቀሪው እንደገና ለማእከላዊ ቀመር ተካፍሎ፣ የዚህም ቀሪ እንደገና ለንኡስ ቀመር ተካፍሎ ከውጤቱ ባሻገር የሚገኘው ትርፍ/ቀሪ ነው፡፡

★ የ2014 ዓ.ም መደብ
→ ዓመተ ዓለም / ዐቢይ ቀመር = 7514/ 502 = 14 ደርሶ 486 ይቀራል፤

→ ቀሪው/ ለማእከላዊ ቀመር = 486/76 = 6 ጊዜ ደርሶ 30 ይቀራል፤

→ ቀሪው / ለንኡስ ቀመር = 30/19 = 1 ደርሶ 11 ይቀራል፤

★ ስለዚህ የ2014 ዓ.ም መደብ 10 ነው፡፡

✥ ወንበር፦ ማለት ደግሞ ዓመተ ዓለም ለንኡስ ቀመር ተካፍሎ ከውጤቱ ባሻገር ከሚገኘው ቀሪ ላይ 1 ሲቀነስ የሚገኘው ውጤት ነው፡፡

★ የ2014 ዓ.ም.ወንበር
→ 7514 / 19 = 395 ደርሶ 9 ይቀራል

→ 9 – 1 = 8

★ ስለዚህ የ2014 ዓ.ም ወንበር 8 ነው፡፡

✥ መጥቅዕ፦ ማለት ነጋሪት ማለት ነው፡፡ ነጋሪት ሲመታ ሕዝብ አንደሚሰበስብ በመጥቅዕ የተሰየመው ዕለት ደግሞ አጽዋማትንና በዓላትን ስለሚሰበስብ መጥቅዕ ይባላል፡፡ መጥቅዕን ለማግኘት የዘመኑን ወንበር በ19 በማባዛት ውጤቱ ከ30 ቢበልጥ ለ30 ከተካፈለ በኋላ የሚገኘው ትርፍ የዘመኑ መጥቅዕ ይሆናል፡፡ ከ30 ባይበልጥ ግን የተገኘው ውጤት የዘመኑ መጥቅዕ ይሆናል፡፡

★ የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ = የ2014 ዓ.ም ወንበር X 19 = 8 X 19 = 152

→ 152 ከ30 ስለሚበልጥ ለ30 እናካፍለዋለን።
→ 152 / 30 = 5 ደርሶ 2 ይቀራል፤

★ ስለዚህ የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ 2 ነው።

✥ መጥቅዕ ከ14 ከበለጠ በመስከረም፣ ከ14 ካነሰ በጥቅምት ይውላል፡፡

❖ የዘንድሮው መጥቅዕ 2 በመሆኑና ከ14 በማነሱ የሚውለው በጥቅምት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ ጥቅምት 2 ነው፡፡ የ2014 ዓ.ም ጥቅምት 2 የዋለው ማክሰኞ ዕለት ነበር፡፡

✥ የዕለታት ተውሳክ፦ ማለት ምን እንደሆነና ከየት እንደተገኘ ለማወቅ አንባቢን ከመጻሕፍት እንዲያነብ በመጋበዝ የዕለታት ተውሳክን እንጠቁም።

√ የቅዳሜ ተውሳክ 8 ነው፤
√ የእሑድ ተውሳክ 7 ነው፤
√ የሰኞ ተውሳክ 6 ነው፤
√ የማክሰኞ ተውሳክ 5 ነው፤
√ የረቡዕ ተውሳክ 4 ነው፤
√ የሐሙስ ተውሳክ 3 ነው፤
√ የዓርብ ተውሳክ 2 ነው፡፡

✥ መባጃ ሐመር፦ በዓለ መጥቅዕና የበዓለ መጥቅዑ ዕለተ ተውሳክ ተደምረው የሚገኘው ውጤት ከ30 ባይበልጥ መባጃ ሐመር ይባላል፡፡ የበዓለ መጥቅዑና የዕለቱ ተውሳክ ተደምረው ድምሩ ከ30 ቢበልጥ ከድምሩ ላይ 30 ተቀንሶለት ተራፊው መባጃ ሐመር ይባላል፡፡ መባጃ ሐመር ጾመ ነነዌን ለማግኘት የሚያገለግል ቁጥር ነው፡፡

★ የ2014 ዓ.ም መባጃ ሐመር
→ የ2014 ዓ.ም መጥቅዕ + የመጥቅዑ ዕለተ ተውሳክ
(የመጥቅዑ ተውሳክ 5 ነው ምክንያቱም ጥቅምት 2 ማክሰኞ ስለዋለና የማክሰኞ ተውሳክ ደግሞ 5 ስለሆነ ነው፡፡)

→ 2 + 5 = 7
★ ስለዚህ የ2014 ዓ.ም መባጃ ሐመር 7 ነው፡፡

✥ በመሆኑም የ2014 ዓ.ም ጾመ ነነዌ በየካቲት 7 ይገባል ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነነዌ አንዴ ከተገኘ ሌሎቹን አጽዋማትና በዓላት በመደመር ብቻ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡

✥ የ2014 ዓ.ም ዐቢይ ጾም የሚገባው መች እንደሆነ ለማወቅ ቀደም ሲል «ዐቢይ ጾም ነነዌ በገባ በ14ኛው ቀን ይገባል» ስላልን ከነነዌ ተነሥተን በመቁጠር ማወቅ እንችላለን።

• የ2014 ዓ.ም ዐቢይ ጾም መግቢያ = የካቲት 7 + 14 = የካቲት 21

• የ2014 ዓ.ም ደብረዘይት = የካቲት 7 + 41 = መጋቢት 18
• የ2014 ዓ.ም ሆሣዕና = የካቲት 7 + 62 = ሚያዝያ 9
• የ2014 ዓ.ም ስቅለት = የካቲት 7 + 67 = ሚያዝያ 14
• የ2014 ዓ.ም ትንሣኤ = የካቲት 7 + 69 = ሚያዝያ 16
• የ2014 ዓ.ም ርክበ ካህናት = የካቲት 7 + 93 = ግንቦት 10
• የ2014 ዓ.ም ዕርገት = የካቲት 7 + 108 = ግንቦት 25
• የ2014 ዓ.ም በዓለ ኀምሳ (ጰራቅሊጦስ) = የካቲት 7 + 118 = ሰኔ 5
• የ2014 ዓ.ም ጾመ ሐዋርያት = የካቲት 7 + 119 = ሰኔ 6
• የ2014 ዓ.ም ጾመ ድኅነት = የካቲት 7 + 121 = ሰኔ 8
አጽዋማቱንና በዓላቱን የበረከትና የረድዔት ያድርግልን፡፡


መሠረተ፡ግእዝ
@learnGeez1
@learnGeez1
@learnGeez1