Get Mystery Box with random crypto!

እብዱ ደራሲ ክፍል አንድ በመغፊራ ቢንት ፉላን ........... ለመኖርም ለመሞትም አልታደለ | KIRAMI

እብዱ ደራሲ ክፍል አንድ
በመغፊራ ቢንት ፉላን
...........
ለመኖርም ለመሞትም አልታደለም በመኖር ውስጥ የሞተ፣ ሞተ እየተባለ የኖረ፣ ምስኪን ፍጡር ነው።የማያውቁት ሰዎች ከሩቅ ሲያዩት በፍርሀት ልባቸው ጥለው ይሮጣሉ ከፊሉ መንገድ ይቀይራል፣ከፊሉ በፍርሀት ይጨማደዳል፣ የሚያውቁት ደሞ ከፊሉ እያዘነለት፣ ከፊሉ እያዘነበት፣ በአጠገቡ ማለፍ ሳይሳቀቅ፣ እንዳላወቁት ሳይደነግጥ በአጠገቡ ያልፋሉ።ሁሌ ከእጁ ላይ የማትለየዋ ቡኒ ተስቢህ የማሂር መታወቂያ ነች ሲቀመጥ ሲነሳ ሲተኛ ሲበላ ሁሌም እጁ ላይ አለች። ሲዞር ሳንቲም ሲለቅም ይውል እና የሰፈሩ ወጣቶች በሸራ እና በማዳበሪያ የሰሩለት ቤት ውስጥ ሄዶ ይተኛል። የተቦጫጨቀ ልብሱ እላዩ ላይ ሊያልቅ ትንሽ ቀርቶታል ከማይታየው የሰውነት ክፍሉ የሚታየው ይበዛል ያለፈ ያገደመውን ሳንቲም ይጠይቃል። ግማሹ በሀዘኔታ,ግማሹ ብከለክለው ይመታኝ ይሁን በሚል ፍራቻ, ይሰጡታል። አንድአንድም አለ ሂድ ከዚ! ብሎ ቀልቡን ገፎ የሚያባርረው፧ ለነገሩ ማሂር ቀልብ የለውም! ቀልብ ቢኖረውማ የተቦጫጨቀ ልብሱን በቀየረ፤መንገድ ማደሩን ትቶ ወደቤቱ በገባ፤ ግን የት ነው ቤቱ? ከየትስ ነው የመጣው? ለምንድነው አብዛኛውን ጊዜ እዚህ ሰፈር የሚኖረው? እንደዚ ሲሆን ጠያቂ የለውም? ና ልጄ ብላ የምትሰበስብ እናት ወይ የሚሰበስብ አባት የለውም? ቤተሰቦቹስ? ዘመዶቹስ? የማን ልጅ ነው? ወደ ሰፈሩ የመጣ አዲስ ነዋሪ ፤ለእንግድነት የመጣ ሳይቀር የሚጠይቀው ጥያቄ ነው፤ግን መልስ የለም። ማሂር እዚ መንደር መቶ መዋል ማደር ከጀመረ አምስት አመታትን አስቆጥሯል አንዳንዴ ለተወሰኑ ቀናት ከመንደሩ ይጠፋል ግን እሰይ ተገላገልን የሚለው የለም፡፡ሁሌም አንድሳምንት ቆይቶ ይመጣል የት ይሂድ?ለምን ይሂድ? የሚያውቅ የለም! የመንደሩ ሰው እንደጎረቤቱ ለምዶታል፧ከአይናቸው ሲጠፋ ባይፈልጉትም ይጠይቃሉ የት ሄዶ ይሆን?ብለው ይጨነቃሉ! መኪና ገጭቶት ይሆን? እብድ ነው ብለው ቀጥቅጠውት ይሆን? ማሂር እኮ ግን እብድ አደለም! ሰው አይናካም የጫት ሱስ የለበትም ሰው አያሰቸግርም አይጮህም እንደ እብድ አይለፈልፍም! ትልቅ ሰው ይወዳል እቃ ተሸክመው ካየ ተቀብሏቸው የሚፈልጉበት ቦታ ያደርስላቸዋል። አሁን አሁንማ እነሱም ና እስቲ የኔ ልጅ ይሄን እቃ አድርስ!እያሉ ይልኩት ጀምረዋል። እንቢ አያውቅም አንገቱን እንዳቀረቀረ የተባለበት ቦታ ያደርሳል። የሰፈሩ ጎረምሶች እብዱ ደራሲ ይሉታል ያገኘው ነገር ላይ ይፅፋል ለሰው የማይገባ ለሱ እረፍት የሚሰጠው አይነት ፁሁፍ ወጣቶቹ ይወዱታል እሱም ሳንቲም እንዲሰጡት ስለሚፈልግ ሲያዙት ይታዘዛል እነሱም እጃቸው ለሱ ይዘረጋል ደሞ ብር አይቀበልም ሳንቲም ብቻ፤ ለሊት በሱ አጠገብ ያለፈ ሰው ሳንቲም ሲቆጥር ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል፡ምን እንደሚያደርግበት ባያውቁም ይሰጡታል እሱም ይሰበስባል። ህፃናት የሚጫወቱበት ቦታ ላይ አይጠፋም አንድሰሞን ሲመጣ እየፈሩ ይሮጡ ነበር አሁን ይቀርቡት ጀምረዋል አንዳንዴ አብሯቸው ይጫወታል ያጫውታቸዋል አብሯቸው ይስቃል በሳቁ ውስጥ ግን ሁሌም እንባ አለ ቶሎ የማይደርቅ እንባ ሀዘን ስብራት እንዳዘለች የምታስታውቅ እንባ ያነባል ተስፋ የቆረጠ ናፍቆት ያጠቃው ብቸኝነት ያጎሳቆለው ሰው የሚያፈሰውን እንባ እንደጎረፍ ያዘንበዋል ማልቀስ ከጀመረ አያቆምም ግን እሱ እየሳቀ ነው ሚያለቅሰው! ሳቁ ደሞ ከጣራ በላይ ይሰማል፤ ሰዎች ሲያለቅሱ ደሞ ይስቃል፤ ሰፈር ውስጥ ለቅሶ ካለ እዛ ከአካባቢ አይጠፋም ሰዎች በሀዘን እንባቸውን ሲያወርዱ እሱ ግን በደስታ በሚመስል መልኩ ይስቃል በደስታ እንደሚቦርቅ ህፃን ይፈነድቃል እንግድነት ለመጣው ሰው አዲስ ነገር ቢሆንም መንደሩ ግን ይሄን ለምዶታል እና ተውት እብድ ነው ይባላል ።ሰዎች እብድ ነው የሚሉት እቤታቸው አስገብተው ሊያኖሩት የሚፈሩት ዋናው ምክንያታቸው ይሄ ነው። ዛሬ ግን ማሂር የለም እናቶች እንደህፃን የሚልኩት ህፃናቶች የጨዋታ ማድመቂያቸው ወጣቶቹን ሳንቲም እያለ የሚለምናቸው የፈለጉት ቦታ የሚልኩት ማሂር ዛሬ ቦታው የለም። እንደለመደው አንድ ሳምንት ቆይቶ ይመጣል ብሎ ሁሉም እየጠበቀ ነው። እሱ ግን የለም እናት ልጇ ወቶ እንደቀረባት ልጅ ከስራ ሲመጣ ብስኩት ገዝቶ እንደሚያመጣለት አባት ደጅ ደጁን እያዩ ነው አረ ባካቹ እብዱ ደራሲ እኮ ከጠፋ ሳምንት አለፈው እያሉ የወንድማቸውን ያህል የሚጨነቁለት ጎረምሶቹ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።ማሂር ግን የለም ........
ክፍል ሁለት ይቀጥላል.....