✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳት #እናቶቻችን #አትናስያ_እና_ኢዮዸራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ ✞✞✞ #ቅድስት_አትናስያ ✞✞✞ =>የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- +ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም #መኑፍ በሚባል አውራጃ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ:: +ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ: እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: #መንፈስ_ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች:: +መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች:: +ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት: ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች:: +በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር:: በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ:: +እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ" ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም #ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው:: +የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች:: +ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም #ቅዱስ_ዮሐንስ_ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነውና:: +እነርሱ ሱባ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ:: "እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ ቀረባት:: (መዝ. 22) +ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች:: +ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች:: +ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ:: +መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ #መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: "የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ #አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ:: +ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: 7 ጊዜ ይነሳል::" +"+ #ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ ድንግል +"+ =>ይህቺ ቅድስት እናት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔው የገባችው ገና በ6 ዓመቷ ነው:: አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮዸራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብፅ ገዳማት ይሔዳሉ:: በዚያ #ደናግል ጌታችንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች:: +ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት:: የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች:: እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሂድ" ብትላትም ያቺ የ6 ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም" አለቻት:: +እናት የሕጻን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሺው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላም እናት ታማ ዐረፈች:: ቅድስት ኢዮዸራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች:: +ትዕግስት: ትሕትና: ፍቅር: ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ:: እህል የምትቀምሰው በ7 ቀን አንዴ ብቻ ሆነ:: ለጸሎት ስትቆምም እስከ 40 ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር:: ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት:: +በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር:: እርሷ ግን ታገሰችው:: እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች:: በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግስቱ በቃች:: ድንግል #ኢዮዸራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ:: =>የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው: ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን:: =>ነሐሴ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅድስት አትናስያ ቡርክት 2.ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል 3.ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት =>ወርኀዊ በዓላት 1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት 2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ 3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ 4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ) 5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ 6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ 7.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት) =>+"+ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ:: +"+ (1ጢሞ. 1:15) > @kiidane 4 viewsedited 21:05