Get Mystery Box with random crypto!

ከህይወት ገጽ ፭ ... 'መስጠት...መቀበል!' 'መስጠትም ከመቀበል ነው፣ መቀበልም ከመስጠት | ኬልቅያስ

ከህይወት ገጽ ፭ ... "መስጠት...መቀበል!"


"መስጠትም ከመቀበል ነው፣ መቀበልም ከመስጠት ነው!"...

ያለንን መስጠት 'አገልግሎት' ነው።

ለካ ስንነጠቅ አብሮ እሚሰጠንም ነገር አለ!።

" አንድ ሰው አስር ክፍል ቤት ሠርቶ ብቻውን ሲኖር አንድ ቀን በሩ ተንኳኳ፤ ሲከፍት ጌታ ነው። "ውይ አምላኬ ጌታዬ አንተ እኔ ቤት መጣህ?" ብሎ በደስታ 'ተቀብሎት' አንድ ክፍል ቤት ሰጥቶት መኖር ጀመሩ። በሌላ ጊዜ በሩ ተንኳኳ፣ ሲከፍት ሰይጣን ነው፤ ይዘጋና ጌታዬ ሆይ አንተ እኔ ቤት እያለህ ሰይጣን የእኔን ቤት እንዴት ያንኳኳል? አለው። ጌታም "ቤቱ የአንተ እንጂ የእኔ አይደለም" አለው። ያሰውም አስቦ ሁለት ክፍል ቤት ለጌታ ጨምሮለት እርሱ ሰባት ክፍል ይዞ መኖር ቀጠሉ። በሩ ተንኳኳ ሲከፍት ሰይጣን ነው። ተበሳጭቶ ይዘጋና "ጌታዬ ሆይ አንተ እኔ ቤት እያለህ ሰይጣን የእኔን ቤት እንዴት ያንኳኳል?" አለው። ጌታም ቤቱ የአንተ እንጂ የእኔ አይደለም አለው። ያሰውም ተሰምቶት ከጌታ ጋር እኩል ለእኩል ተካፈለ፤ ነገር ግን ቤቱ ከቀድሞ ይልቅ ተንኳኳ። አዝኖም ይዘጋና ጌታ ሆይ..?! አለው። ጌታም የቀድሞውን መልስ ሰጠው። በዚህ ጊዜ ይህሰው ለራሱ አንድ ክፍል ቤት ይዞ ዘጠኙን ክፍል ቤት ለጌታ ሰጠው፤ ነገር ግን ከቀድሞው ይልቅ እጅግ በጣም ተንኳኳ። ቢከፈት ሰይጣን ነው። በሩን ይዘጋና ወደ ጌታ ሄዶ "ጌታ ሆይ ምስጢሩ ምንድነው?" አለው። "ጌታ ግን ቤቱ የአንተ እንጂ የእኔ አይደለም"አለው። በዚህ ጊዜ አስሩንም ክፍል ለጌታ አስረከበ። ጌታም መልሶ 'ሰጠው' እና መኖር ጀመሩ። በሩም ተንኳኳ፤ ጌታም ሊከፍት ተነሳ። ሲከፍት ሰይጣን ነው። ሰይጣንም "ይቅርታ የአንተ ቤት መሆኑን አላወቅሁም!" ብሎ ሄደ። ከዚያን ቀን ጀምሮ መንኳኳት አቆመ።
"ሁሉንም የህይወታችንን ክፍል ለጌታ እግዚአብሔር ካላስረከብነው መንኳኳት አይቆምም!።" 10% ስንሰጥ ይንኳኳል። 30% ስንሰጥም ይንኳኳል። 50% ስንሰጥ ይበልጥ ይንኳኳል። 99% ስንሰጥ እጅጉን ይንኳኳል። 100% ስንሰጥ መንኳኳት ያቆማል። እኛ ከከፈትን ሰይጣን ይገዳደረናል፤ ጌታ ሲከፍት ግን "ይቅርታ ቤቱ ያንተ መሆኑን አላወቅሁም" ብሎ ይሄዳል።
እግዚአብሔር ሰማይን የደስታ አገር ያደረጋት ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ የጸናባት በመሆኗ ነው። በእኛም ህይወት የእግዚአብሔር ሰላምና ደስታ የሚመጣው በህይወታችን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንፈጽም ነው። ስለዚህ:- "እግዚአብሔርን እረኛችን እናድርገው!....በፍፁም ልባችን እንከተለው!...የሚያስፈልጉንም ነገሮች እኛን ይከተሉናል!።" ሙሉ ህይወታችንን ለእግዚአብሔር እንስጥ፤ ህይወትን እንቀበላለን።

አንተን ያላንተ ቸርነት ማን መቀበል ይቻለዋል?!....

የሚጠሉትን መስጠት አይከብድም፤ የሚወዱትን መስጠት ግን ፍቅር ነው።

መስጠት መሰጠትንም ጭምር ያካትታል...ይኽም ማለት እራስን አሳልፎ መስጠት ነው።

"ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና!..............።"
(ሉቃስ 6:38-45)
በተለያየ መልኩ ከተማርኩት
አንቆጳጊዮን