Get Mystery Box with random crypto!

ዝም እንድል አድርገኝ በዚህ ኡኡታ ዓለም ምልልስ በበዛው ይሰቀል በሚል ድምጽ ሁከት በከበበው | ኬልቅያስ

ዝም እንድል አድርገኝ

በዚህ ኡኡታ ዓለም ምልልስ በበዛው
ይሰቀል በሚል ድምጽ ሁከት በከበበው
የአይሁድ መንደር ውስጥ ቀን ላስገኘኝ ለኔ
ዝም እንድል አድርገኝ እንዳይጨልም ቀኔ።

አውቃለሁ አምላኬ ቸሩ ንጉስ ጌታ
ከግርግርታው ማየል ካለው ከጫጫታ
የዝምታ ጩኸት እንዲበልጥ ዝምታ
ግና
ነፉስ ለምከተል ጉምን ለተደገፍኩ
ከሚጮሁት ስጮህ ቀናቶቼን ለጣልኩ
በዝምታ ጩኸት እንድጮኽ አድርገኝ
መናገርን ልጣል ዝምታን እንዳገኝ።

እውነትን ለብሰዋት ካሸበረቁቱ
ደምረኝ ከነርሱ ንጉስ ሆይ አቤቱ።
ሀሰትን ለብሰዋት አንተን ከረሱቱ
ጠብቀኝ ከነዚያ ሸንጋዮች አቤቱ።

መቃብርን ምሶ እውነትን ለመቅበር
ሰው ሆ ብሎ ወቷል ለመጣላት ከግዜር
ነጭ ይላል ጥቁሩን አይኔን ግንባር ያርገው
አይኑ ግንባር ሆኖ ጭራሽ እንዳያየው

እኔ ግን ተጥዬ ብቻዬን ምን ብቀር
እውነትን አልልቀቅ ከርሷ ጋር ልቀበር
ከሀሰት መንደር ልራቅ ከሸንጋዮች ጎራ
ዝም እንድል ከእውነት ጋር ልኑር ከርሷ ጋራ

እኔው ተናግሬ ሰሚ እኔው ከሆንኩኝ
ሌላውን አልረብሽ ዝም እንድል አድርገኝ።