Get Mystery Box with random crypto!

በወቅታዊ ጉዳዮች ከማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት የተላለፈ መልእክት ማኅበረ ቅዱሳን በኢ/አ/ተ/ቤ/ን ቅ | ዘማሪ ክብሮም

በወቅታዊ ጉዳዮች ከማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት የተላለፈ መልእክት

ማኅበረ ቅዱሳን በኢ/አ/ተ/ቤ/ን ቅዱስ ሲኖዶሶ በ1984 ዓ.ም እውቅና አግኝቶ በ1994 ዓ.ም በጸደቀለት ሕገ ደንብ መሠረት አገልግሎቱን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም የቅድስት ቤተክርስቲያን ዐቢይ ተልዕኮ የሆነውን የእግዚአብሔርን ወንጌለ መንግሥት በስፋት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ እንዲዳረስ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በየጊዜው ያጋጠሙትን ፈተናዎችን እግዚአብሔር ቸርነት በከፍተኛ ትጋትና ጽናት ያለፈ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው።

ማኅበሩ ካሉት የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የብሮድካስት አገልግሎቱ ሲሆን፤ በ2012 ዓ/ም የተጀመረው ይህ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያሰራጨው የወንጌል አገልግሎት በመላው ምእመን ዘንድ አማራጭ ሚዲያ ከመሆን አልፎ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው የየዕለት ስንቅ በመሆን በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ እንደ ዐይን ብሌን የሚጠብቁት ሚዲያ ለመሆን በቅቷል።

የብሮድካስት አገልግሎት ልዩ ጥንቃቄ የሚሻ ሥራ ከመሆኑም በተጨማሪ ማኅበራችን አገልግሎቱን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና መንፈሳዊ ቅኝት የሚያከናውን በመሆኑ ሁሌም ምስጉንና የተከበረ ጣቢያ መሆኑን ምእመናን ሁሉ የሚመሰክሩት እውነታ ነው።

በዚህ መነሻነት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሜቴ ያዘጋጀውን መግለጫ በማስተላለፋችን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ "ጊዜያዊ እገዳ" ማድረጉን ገልጾልናል፡፡

ባለሥልጣን መ/ቤቱ ለጊዜያዊ እገዳ የሰጠው ምክንያት ማኅበሩ ከተቋቋመለት ዓለማ ውጭ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እንኳን ሊያሳግድ ይቅርና ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ማኅበሩ ይረዳል። የእግዱ ሂደትም የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን ያልተከተለና የሚዲያውን አገልግሎት በጸሎት፣ በገንዘብና በእውቀታችሁ በመደገፍ ሊዚህ ያበቃችሁትን ካህናት፣ ምእመናንና አባላትን ያሳዘነ መሆኑን ተረድተናል፡፡

በመሆኑም እግዱ የምእመናን ድምጽ የሚያፍን ብሎም ትምህርተ ወንጌልን የመማር መብታቸውን የሚገድብ መሆኑን በማሳወቅ ለሚመለከተው አካል አቤቱታውን በደብዳቤ አቅርቧል። አቤቱታውም በአግባቡና በሕጉ መሠረት ታይቶ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠው ተስፋ እናደርጋለን። እንዲሁም ማኅበራችን ጉዳዩ የሕግ አግባብን ተከትሎ ውሳኔ እስከሚያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲገነዘብልንና ይህንኑ በየጊዜው በይፋ የምናሳውቅ ስለሆነ በታላቅ ትዕግሥት አንዲጠብቅ እንጠይቃለን።

በዚህ አጋጣሚ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ስለ ጉዳዩ በተፈጠረባችሁ ቁጭትና ከፍተኛ የቁጣ ስሜት የቤተክርስቲያንን መብት ለማስከበር ለምታደርጉት ተነሳሽነት ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ከፍተኛ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦቱ ርክበ ካህናት ስብሰባ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም ባደረገው ምልአተ ጉባኤ ችግር ባለባቸውና አስፈላጊ በሆኑ አኅጉረ ስብከቶች ፱ አዳዲስ ኤጴስ ቆጶሳትን በጥናት ለመሾም አስመራጭ ኮሜቴ መሰየሙ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የምርጫ ሄደቱም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ፣ ግልጽነት ያለው፣ ካህናትና ምእመናንን ያሳተፈ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡