2022-06-30 13:14:56
የተመረቀው ብቸኛው መንገድ
የሰው ልጅ ትዕዛዝ ከመተላለፉና ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት
የሚከተሉት ሦስት እድሎች ነበሩት፡፡
ሀ) ያለምንም መከልከል ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግና
ኀብረት ማድረግ ይችል ነበር፡፡
ለ) ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ግንኙነትና ኅብረት የተነሳ ፈጣሪውን
ያውቅ ነበር፡፡
ሐ)ምድራዊ ኑሮ መኖር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወት ነበረው፡፡
የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላልፎ ኃጢአት ባደረገ ጊዜ ግን ሰው
እነዚህን ከላይ የዘረዘርናቸው ዕድሎች ሁሉ አጣቸው፡፡ በዚህ
ምክንያት እነዚህን ዕድሎች መልሶ ለመጐናፀፍ ሦስት ዓይነት ነገሮች
አስፈለጉት፡፡ እነርሱም፥
ሀ. እርቅ
፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ኃጢአት የፈጠረው ርቀት
ተወግዶ እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ የሚያስችል መንገድ
አስፈለገው፡፡
ለ. መንፈሳዊ ብርሃን
፥ ሰው በአእምሮ ብቻ ስለ እግዚአብሔር ማወቁ
ቀርቶ እግዚአብሔርን በግል ሕይወቱ ለማወቅ መንፈሳዊ ጨለማውን
የሚገፍለትን ትክክለኛውን መረዳት የሚሰጠው ብርሃን አስፈለገው፡፡
ሐ. አዲስ ልደት፥ ሰው መንፈሳዊነትን ለማግኘት ከመንፈስ ቅዱስና
ከእግዚአብሔር ቃል እንደገና መወለድ አስፈለገው፡፡
ለብዙ ሺህ ዘመናት ሰው እነዚህን ፍላጐቶቹን ማሟላት የሚችልለት
ሳያገኝ ቀረ፡፡ ስለዚህ ሰው ለችግሩ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ሳያገኝ
ኖረ፡፡ ነገር ግን ጊዜውና ሰዓቱ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን
ኢየሱስ ክርስቶስን ለዚሁ ዓላማ መርቆና ሹሞ ወደዚህ ዓለም ላከለት፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ ያስተማራቸው
ትምህርቶችና ያበሰራቸው የምሥራች አዋጆች እንዲሁም በመስቀል
ላይ የሰራው ሥራ ከላይ የተገለጸውን የሰው ዋና ፍላጎቶች የሚያሟላ
ነበር፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቁጥር 6 ላይ እንደምናነበው፤
“ኢየሱስም፥ እኔ መንገድና ዕውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ
አብ የሚመጣ የለም፤” አለ፡፡
ሀ.“እኔ መንገድ ነኝ።” ሲል ሰው ወደ እግዚአብሔር መምጣት
የሚችልበት የተመረቀው ብቸኛ መንገድ እርሱ ብቻ መሆኑን መግለጹ
ነው፡፡ በሌላም ቦታ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጐች
በር ነኝ” ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐንስ 10፥7)ከእርሱ ሌላ ወደ
እግዚአብሔር መምጣትና እርቅ ማድረግ አይቻልም፡፡
ለ.“እውነት ነኝ።” በማለቱ ደግሞ የሰውን የአዕምሮ ጨለማ
የሚገፍ ብርሃን (እውነት) እርሱ ብቻ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ሰው
እግዚአብሔርን ማወቅ የሚችለው በግል ኢየሱስን በማወቅ ብቻ ነው፡፡ (ዮሐንስ 14፥9)
ሐ.“ሕይወት ነኝ” ሲል ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ
ከመንፈስ ቅዱስና ከቃሉ ዳግመኛ በመወለድ አጥቶት የነበረውን
ዘላለማዊና መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሚያገኝ ለመጠቆም ነው፡፡
ሐዋርያትም ሌላ ሳይሆን እርሱ ራሱ ክርስቶስ “ነኝ” ሲል ያወጀውን
ቃል አምነው በመቀበል “መዳን በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ
የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ከሰማይ በታች ሌላ ስም የለምና፡፡”
(የሐዋርያት ሥራ 4፥12) በማለት የእርሱን ብቸኛ መድኃኒትነት
አውጀዋል፡፡
የሰውንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት በተመለከተ ጉዳይ በመካከል ሆኖ
ሰውንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ የሚችል ክርስቶስ ብቻ መሆኑ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግሞ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ “አንድ
እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው
መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፣ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፡፡”(1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5)
ከእርሱም ሌላ በመስቀል ላይ ደሙን ለሰው ልጆች ደህንነት ያፈሰሰ ማንም የለም፡፡
አንዳንድ ሰዎች ከተሾመው ብቸኛ መንገድ ሌላ ምርጫ ያለ እየመሰላቸው “እኛ የምናምነው እምነት …” እና “እናንተ ደግሞ
የምታምኑት እምነት …” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ አንድ ነገር እውነት
የሚሆነው እኛ ስላመንበት አይደለም፡፡
ሰው በአንድ ነገር ማመን ያለበት ያ ነገር እውነት በመሆኑ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ
አንድ ሰው መሬት ጠፍጣፋ ነች ብሎ ቢያምን የእርሱ እምነት መሬት ክብነቷን ትታ ጠፍጣፋ እንድትሆን አያደርጋትም፡፡ መሬት ክብ እንደሆነች የምናምነው በመጽሐፍ ቅዱስም የተደገፈ ሳይንሳዊ ሐቅ በመሆኑ ነው፡፡
እምነት “የሚያድን እምነት”የሚሆነው እምነታችንን ከምናደርግበት ነገር ማንነት የተነሳ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ተማሪ አንዱን ዛፍ
ጆዖግራፊ አስተምረኝ ብሎ ቢያምንበትና ቢጠመጠምበት ዛፉ
ጆዖግራፊ ሊያስተምረው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ዛፍ ጆዖግራፊ የማስተማር ችሎታ የለውም፡፡ ልክ እንደዚሁ ከተመረቀው ብቸኛ
መንገድ በቀር ደህንነትን የሚሰጥ ሌላ አማራጭ እንዳለ መድከም
ከንቱ ድካም ብቻ ነው፡፡
ሰው ደህንነትን በተመለከተ የሚያደርገው ምርጫና ውሳኔ አይስክሪም ለመግዛት ከሚያደርገው ምርጫና ውሳኔ የተሻለ ሊሆን ይገባል፡፡ አንድ
ሰው አይስክሪም ሲገዛ የሚመርጠው እርሱ የወደደውንና የፈቀደውን ነው፡፡ ነገር ግን አይስክሪም ለመግዛት ያደረገውን ምርጫና ውሳኔ መድኃኒት ለመግዛት ቢያስፈልገው ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ ሰው
መድኃኒት የሚገዛው ደስ የሚለውን በመምረጥ ሳይሆን ከህመሙ ሊያድነው የሚችለውን ብቻ ነው፡፡ የነፍስ ደህንነትም ጉዳይ የሚመሰረተው በመድኃኒቱ ፍቱንነት ላይ እንጂ ሰው በወደደውና “ያድነኛል” ብሎ በመረጠው ምርጫ ላይ አይደለም፡፡
አንዳንድ ሐኪሞች በሽተኞቻቸውን መርምረው ምንም በሽታ ሳይገኝባቸው ሲቀርና፤ “ያመኛል እስቃያለሁ” ማለታቸው የማያቆም
ሲሆን ጉዳዩ የበሽታ ሳይሆን በአእምሮ ያለ የሐሳብ ጉዳይ ነው ብለው በመገመት ‘ፕለሲቦ’ የተባለ መድኃኒት ያዙላቸዋል፡፡ ‘ፕለሲቦ’ መድኃኒት ሳይሆን በመድኃኒት መልክ የተሰራ የስኳር እንክብል ነው፡፡
በሸተኞቹም ለበሽታው መድኃኒት ተገኘ ብለው ያንን ‘ፕለሲቦ’
ውጠው ከበሽታቸው የዳኑ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን የስሜትና
የአስተሳሰብ ነገር እንጂ ‘ፕለሲቦ’ ምንም መድኃኒትነት የለውም፡፡
እንደዚሁም ከተመረቀው ብቸኛ መንገድ (ከክርስቶስ)በቀር ደኅንነት
የሚገኝበት መንገድ የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ
የዓለም መድኃኒት (መድኃኒዓለም) እንደሆነ በማመንና “መድኃኒቴ”
ብሎ እርሱን በመቀበል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ልዩነቱም
የመጀመሪያውን አጋንንትም እንኳ ስለማይክዱትና ስለሚናገሩት ሲሆን
ሁለተኛውን ግን በግል ሕይወቱ መድኃኒትነቱን የቀመሰና ያወቀ ሰው ብቻ ለማለት ስለሚችለው ነው፡፡
ቀደም ሲል ላነሳነው ዋና የነፍስ ፍላጐትዎ ብዙ ባለመድኃኒቶች
ሞክረው መፍትሔ አላገኙም ይሆናል፡፡ ካላገኙ ለምን የተመረቀውን ብቸኛ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን አይሞክሩም?
“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም
አሳርፋችኋለሁ፡፡” (ማቴዎስ 11፥28)
https://t.me/IWNRSATT
110 viewsSintayehu Nigatu, 10:14