Get Mystery Box with random crypto!

ከራስህ አትሽሽ! ከእውነትህ ተፋጠጥ፤ የሰቀልከውን እውነት አውርድ! (Face the reality!) | የስብዕና ልህቀት

ከራስህ አትሽሽ! ከእውነትህ ተፋጠጥ፤ የሰቀልከውን እውነት አውርድ!
(Face the reality!)
(እ.ብ.ይ.)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየዓመቱ የሚፆመው የአብይ ፆም ሊገባደድ የአንድ ቀን ዕድሜ ነው የቀረው፡፡ ፆሙ የጌታችንንና የመድሐኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የአርባ ቀንና የአርባ ሌሊት ፆም መታሰቢያ የሚያደርግ ዓመታዊ ፆም ነው፡፡ በተለይ ይሄ ሊያልቅ ያለው ሳምንት የክርስቶስን ህማማቱን፣ ግርፋቱን፣ አንግልቱን፣ ስቃዩን የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ አዎ ጌታችን የሰቀሉትን ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ነፍሱን ቢሰጥም በሶሰትኛው ቀን በመለኮታዊ ሃይሉ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል፡፡ ሞትን አሸንፏል፡፡ ፍቅሩ ምድርን ሁሉ ገዝቷል፡፡

የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ዓለማችን አሁንም እውነትን እንደሰቀለች መሆኗ ነው፡፡ በዚህ በኛ ዘመንና ትውልድ አሁንም ሐቅ እንደተሰቀለ ነው፡፡ በእውነት የሚነግድ ነጋዴ ጠፍቷል፡፡ በታማኝነት ሐገሩን የሚያገለግል ባለስልጣን ህልም እየሆነ ነው፡፡ ዛሬም እውነት በምድራችን ላይ የለችም የሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ እውነት ያለው ፍቅር፣ እውነት ያለው እምነት፣ ሐቅ ያለው ንግድ፣ እውነት ያለው ወዳጅነት፣ እውነት ያለው ዝምድና፣ እውነት የሞላው ትዳር፤ እውነት ያለው ዕውቀት፤ ለእውነት የሚወግን ህግ፣ ለእውነት የቆመ መንግስት፣ በሀቅ የሚመራ የሰው ልጅ እየጠፋ ነው፡፡ በድብብቆሽ የጦፈ የሴሰኝነት ፍቅር፤ በወረት የሞቀ ወዳጅነት፣ በመከዳዳት የሚገባደድ ስምምነት፤ በመሰለቻቸት፣ በመጠላላትና በመጠፋፋት የሚያልቅ ወዳጅነት፤ በውክቢያና በችኮላ ተጀምሮ ግለቱን ቶሎ በሚጨርስ የወረት ፍቅረኝነት ዓለም እየታመሰች ነው፡፡ ሰው በገዛ የምኞት ገመዱ ተጠፍንጓል፡፡ ልቅ ፍላጎቱ መረን ለቅቆታል፡፡ ስሜቱ አዋክቦ ከሕሊናው አርቆታል፡፡ ደመነፍሱ ከራሱ ጋር አጣልቶታል፡፡ ስጋውና ነፍሱ፤ ስሜቱና መንፈሱ አልተዋሃደም፡፡ ለመብላት ብቻ የሚኖር ሆዳም ትውልድ ሆኗል፡፡ ለገዛ ጥቅሙ ብቻ ሲል የሌሎችን መብትና ጥቅም የሚጋፋ ስግብግብ ፍጥረት በዝቷል፡፡ ብልጠት እንጂ ብልህነት የሌለው ትውልድ በገፍ እያመረትን ነው፡፡

በዚህ ዘመን እውነቱንና እምነቱን በአፉ ብቻ የሚናገር ነው ምድሪቱን የሞላው፡፡ ለመናገር የፈጠነ፣ ለመስማትና ረጋ ብሎ ለማስተዋል የዘገየ ነው ዓለሙን ያጥለቀለቀው፡፡ በኑሮውና በሕይወቱ እውነቱንና እምነቱን በተግባር አጥብቆ የያዘ እምብዛም ነው፡፡ ሰውነቱን አሽቀንጥሮ የጣለ፣ ስብዕናው የተቃወሰ እልፍ ነው፡፡ ይሄ ሰልጥኛለሁ የሚለው ዘመነኛው ትውልድ ከህሊናው የተጣላ፤ ፍቃደ-ልቦናውን የዘነጋ፣ እፍረት የሌለው ፈጣጣ ትውልድ ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎቹን መዘርዘር ይቻላል፡፡ አዎ የዛሬው ሰው በገዛ ፍቃዱ በላዩ ላይ የባርነት ቀንበሩን አክብዷል፤ የሎሌነት ሸክሙን አብዝቷል፡፡ የሰለጠነ መስሎት ሠይጥኗል፡፡ ገንዘብ ገንዘብ ሲል ግንዛቤውን ጥሏል፣ ማስተዋሉን አጥቷል፡፡ ሰውነቱን ላይደርስበት አርቆ ሰቅሏል፡፡

ሰው እውነትን ሰቅሎ ኑሮውን አስወድዷል፡፡ የዋጋ ንረቱን ጭንቅላቱን አዙሮታል፡፡ ዘንድሮ ያልተሰቀለ ምን አለ? እውነት ተሰቅሏል፤ እምነት ተሰቅሏል፤ ኑሮ ተሰቅሏል፣ የእህልና የቁስ ዋጋ ተሰቅሏል፣ ሰውነት ላይደረስበት ተሰቅሏል፤ ደግነት ተወድዷል፤ ታማኝነት እንደብርቅዬ እንስሳ የሚታይ ሆኗል፡፡ አጃኢብ ነው መቼስ!

ወዳጄ ሆይ..... ያንተስ የአንተነትህ ፋሲካ መቼ ነው?? ያንተስ የሰውነት ትንሳኤህ ወዴት አለ?? ከቶ መቼ ይሆን ከሃሳብ ህመምህ፣ አስተሳሰብ ስቃይህ የምትገላገለው?? የሰው ልጆችስ ከወደቅንበት ስብዕናችን የምንነሳው መቼ ይሆን??

አዎ ወዳጄ! ከመንጋው ጋር አትጋፋ! በስሜት ከሚነጉደው ጋር አትንጎድ፡፡ የበዓሉን ምሳሌነት ተረዳ፡፡ የምታየውን፣ የምትሰማውን ሁሉ ከሕይወትህ ጋር እያገናኘህ አስበው፣ ተንትነው፣ አብሰልስለው፡፡ ከዛም የሚጠቅምህን ውሰድ፡፡ በጎ ነገርን ተለማመድ፡፡ በሚጠቅም አዲስ ሃሳብ ትለወጥ ዘንድ በርታ፡፡ በስቅለቱ በዓል የተሰቀለውን ክርስቶስ ህማሙን እያስታወስክ ዛሬም አንተን እያሰቃየህ ያለው የምኞት ዓለም እየመረመርክ፤ ራስህ አርቀህ የሰቀልከውን እውነት አውርድና ለእውነትና በእውነት ኑሮህን ጀምር፡፡ የትንሳኤውን በዓል ስታከብር አንተን የጣለህንና የአሸነፈህን ቀሽም አስተሳሰብ ድል ነስተህ በአዲስና በቀና አስተሳሰብ ተነስተህ ሕይወትህን አቅናው፡፡

ከራስህ አትሽሽ! ከእውነትህ ተፋጠጥ፤ የሰቀልከውን እውነት አውርድ - Face the reality!

‹‹ጥንት የተሠቀለችው እውነት
ለልብ አብነት ነች፣
ለሰው ምሣሌ ነች፤
በደምና በአጥንት፤ ታስራ የተገመደች፡፡
ውስጠኛዋን እውነት መላልሶ ለመስራት፣
የተሠቀለችውንም እውነት፤ ያሻል አለመርሳት፡፡››

....የትንሳኤውን በዓል ስታከብር አንተን የጣለህንና የአሸነፈህን ቀሽም አስተሳሰብ ድል ነስተህ በአዲስና በቀና አስተሳሰብ ተነስተህ ሕይወትህን አቅናው፡፡...

መልካም የትንሳኤ በዓል!

____
እሸቱ ብሩ
ይትባረክ

@EshetuBirruYitebarek
@Zephilosophy
@Zephilosophy