Get Mystery Box with random crypto!

“የመገፋት ስስነት” (“የመገፋት ህመም” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ) በስነ-ል | የስብዕና ልህቀት

“የመገፋት ስስነት”
(“የመገፋት ህመም” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

በስነ-ልቦናው ቋንቋ “የመገፋት ስስነት” (Rejection Sensitivity) የተሰኘው ሃሳብ ሰዎች በየእለት ኑሯቸው የሚያጋጥማቸውን ጥቃቅን የሰዎች ሁኔታ ከመገፋትና ከመገለል ጋር የማዛመድ ስስነትንና ዝንባሌን የሚያሳይ ጽንሰ-ሃሳባ ያመለክታል፡፡

አንዳንድ ሰዎች በመገፋት ዙሪያ እጅግ ስስ ከመሆናቸው የተነሳ እንደተገፉ የመሰላቸው ማንኛውም አይነት ሁኔታ ሲመለከቱ የመደናገጥና የመዋረድ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ሰዎች ሲያስጠብቋቸው፣ ስልካቸውን ካልመለሱላቸውና እንደዚህ የመሳሰሉ “አናሳ” የሆኑ ክስተቶች የዝቅተኝትን፣ የመናቅንና የመገለልን ስሜት ያመጣባቸዋል፡፡

“የመገፋት ስስነት” ዝንባሌን አስመልክቶ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የዚህ ተጽእኖ ሰለባዎች፣ ሰዎች በፊት ገጽታቸው የሚያሳዩት ሁኔታ እነሱን ያለመቀበልና የመግፋት ምልክት እንዳለው ሲሰማቸው የአንጎል እንቅስቃሴያቸው (Brain Activity) በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር ጥናቶቹ ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም፣ እነሱን የመግፋት ወይም የማግለል ገጽታ ሊኖረው የሚችልን ማንኛንም እንቀስቃሴም ሆነ ንግግር በንቃትና ሁኔታዎችን በማዛመድ የመመልከትና የመጠባበቅ ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡

የዚህ ዝንባሌ አንዱ ጫና፣ አድልዎ-ተኮር ምላሽ (Attention Bias) ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ለአስር ሰዎች የፍቅር ጥያቄ አቅርበው ዘጠኙ ተቀብለዋቸው አንዱ ብቻ ፍላጎት እንደሌለው ቢገልጽላቸው፣ እነሱ የሚያተኩሩትና ስሜታቸውን የሚነካው የዘጠኙ እሺታ ሳይሆን የአንዱ እምቢታ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ትኩረትን ከመገፋት አንጻር ብቻ የመቃኘት አድሎአዊ አመለካከት የሚያስከትልባቸው የስነ-ልቦና ቀውስ በግል ሕይወታቸውም ሆነ በማሕበራዊ ግንኙነታቸው ላይ የሚስከትለው መዘዝ ቀላል አይደለም (ምንጭ፡- verywellmind.com)፡፡

ሁኔታውን ስንጨምቀው፣ በመገፋት ስቃይ ውስጥ ያለፈ ሰው የሰዎችን፣ በተለይም በእነሱ ሕይወት ስፍራ እንዳላቸው የሚሰማቸውን ሰዎች እያንዳንዱን ተግባር በመገመት በመላ-ምት የመኖር ዝንባሌ ያጠቃቸዋል፡፡ ይህ አሉታዊ-ገማችነት ገደብ የሌለው ሃሳብ-ወለድ አለም ውስጥ እንዲዋዥቁና የሌለንና ያልተፈጠረን ነገር በውስጣቸው እንዲያሰላስሉ ያደርጋቸዋል፡፡

“የመገፋት ስስነት” ያለባቸው ሰዎች አንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት አለም ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲያሰላስሉት ውለው ያደሩት ነገር በእነሱ ውስጥ “የሌለ እውነታ” ሆኖ ይኖራል፡፡ የዚህ ስሜት ውጤት ሰዎች የሚያደርጓቸውንም ሆነ የማያደርጓቸውን ነገሮች እየለቀሙና እየቆጠሩ ካለባቸው “የመገፋት ስስነት” ጋር የማዛመዝ ሁኔታ ነው፡፡

“የመገፋት ስስነት” ያለባቸው ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት በእርግጥም ከእውነተኛ የመገፋት ልምምድ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ለመገፋት ስሜት ስስ እንዲሆኑ ከዳረጋቸው ከእውነታ የራቀ እይታም ሊነሳ ይችላል፡፡ መነሻው ያም ሆነ ይህ፣ ሰዎች በዚህ የስሜት ተጽእኖ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ላለባቸው የስነ-ልቦና ቀውስ ትክክለኛውን መፍትሄ እንዲፈልጉ ይመከራሉ፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence