Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ህንጸተ ቤተክርስቲያን ሰኔ 20 የእ | ኢትዮጵያ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ህንጸተ ቤተክርስቲያን ሰኔ 20
የእመቤታችን ዓመታዊ በዓል ሰኔ 21


የእመቤታችን ዓመታዊ በዓልና በዓለም ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ስለመታነጻቸው፡- ይኽም በዓል ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ‹‹ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን›› ይባላል፡፡ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በሰኔ 20 ቀን ነው፡፡ አናጺውም እራሱ ባለቤቱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው

እመቤታችን ካረገች በ4ኛ ዓመት ጳውሎስና ባርናባስ በፊሊጲስዮስ ገብተው አስተምረው ሕዝቡን አሳምነው ካጠመቁ በኋላ ‹‹እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ›› አሏቸው፡፡ አሕዛብ የነበሩትና አምነው የተጠመቁትም ‹‹የለመድነውን ከከለከላችሁን መካነ ጸሎት ስጡን›› አሏቸው፡፡ የከበሩ ሐዋርያትም ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልእክት ላኩባቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹ያለ ጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባምና ጸልዩ እኛም እንጸልያለን›› ብለው መለሱላቸው

ሁሉም ሱባኤ ይዘው በጸሎት ተጉ፡፡ ጸሎትና ሱባኤያቸውን ከጨረሱ በኋላ ጌታችን በሞት ያረፉትን አስነሥቶ በሕይወት ያሉትንም ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው፡፡ ጌታችን በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን?›› ብሎ ጠየቀ

ጌታችንም ‹‹በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው›› አለው፡፡ ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም ተራርቀው የነበሩ 3 ደንጊያዎች ነበሩ፡፡ ጌታችንም ሦስቱን ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው

ድንጋዮቹም እንደ ሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ለሐዋርያቱ ሠጣቸው፡፡ እነርሱም እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው እየለመለሙ (እየተሳቡ) ቁመቱን 24 ወርዱን 12 ክንድ አድርገው ሠርተውታል፡፡ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ›› ብሏቸው ዐረገ

ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴን ሦስትነት ወደ አንድ ሆነው አንድ ሕንፃ መታጹ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ለኛ ለክርስቲያኖች እጅግ ታላቅ በዓልና ደስታ ነው፡፡ ስለዚች ቤተ ክርስቲያን አባቶች ደማቸውን አፍሰውላታል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተውላታል፣ አጥንታቸውን ከስክሰውላታል፣ ቆዳቸው ተገፏል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በአውሬ ተበልተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዋ ውኃ መሠረቷ ደም ነው፡፡ የማትታደስ ነገር ግን ከኃጢአት ከበደል የሚታደሱባት ርትዕት ናት፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ‹‹የክርስቶስ አካሉና ሙላቱ ናት፡፡›› ኤፌ 1፡13 እናም የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስና ትምህርቷን መቆነጻጸል የክርስቶስን አካል ማድማት ነው

ዳግመኛም በማግሥቱ ሰኔ 21 ቀን ጌታችን ድንግል እናቱን እመቤታችንንና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ወረደ፡፡ እመቤታችንን መንበር፣ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቁርቧቸዋልና ፍጹም ደስታም ሆነ፡፡ ዳግመኛም ጴጥሮስን እጁን ጭኖ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል፡፡ በዚህም ጊዜ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ሐዋርያት አንድ ሆነው አመስግነዋል

ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታችን እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው የእነ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ፣ የአይሁድ ምኩራብ፣ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ሥርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፡፡ እንኪያስ ‹‹ሐዋርያት የት ነበር ሕዝቡን የሚያጠምቁትና የሚያቆርቡት?›› ከተባለ እንደ ማርቆስ እናት ቤታቸው ለሐዋርያት በሰጡ ‹‹በየአማኞቹ ቤት›› ይከናወን ነበር

ሰኔ 20 ቀን ህንጸተ ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መታነጽ) ታላቅ በዓል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሻሽ የመጣችና ሩቅ ብእሲ የመሠረታት ሳትሆን እራሱ ጌታችን አምላካችን በገዛ ደሙ የመሠረታት ናት፡፡ ሐዋ 20፡28፡፡ በዕለተ ዐርብ በዕፀ መስቀል ላይ ከጌታችን የፈሰሰውን ቅዱስ ደም መልዐኩ ዑራኤል በብርሃን ፅዋ ቀድቶ በዓለም ሁሉ ረጭቶታል፡፡ ስለሆነም የጌታችን ወርቀ ደም በነጠበባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይሠራባቸዋል

እንኳን ለእመቤታችን ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ

ምንጭ ፦ ኮኩኸ ሃይማኖት