Get Mystery Box with random crypto!

#በውግዘት___ስም ❸ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬ “ደላንታ የሚባል ሀገር አንድ እጅግ ሀብታም፣ ሀይለኛና | Hasab meda ሐሳብ ሜዳ

#በውግዘት___ስም ❸
▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
“ደላንታ የሚባል ሀገር አንድ እጅግ ሀብታም፣ ሀይለኛና ህዝብ የሚያደንቀው ትዕቢተኛ ሰው ነበር።” ይሉናል ሊቁ ኅሩይ ወልደሥላሴ «የለቅሶ ዜማ ግጥም» በሚል መፅሐፋቸው። ያ ሀብታምና ኅይለኛ ሰው እንደልቡ፣ ሲያስከትል፣ ሲያዝ፣ ሲያስፈፅምና ያሻውን በትዕቢት ሲያደርግ ያስተዋሉ አንድ የሀይማኖት መምህር ወደቤቱ መመላለስና ቀስ በቀስ የመጽሐፍ ቃል ያስተምሩት ጀመሩ። ለዘመናት የገነባው የትዕቢት ዓለት እያደር ተፈረካከሰ። አምላኩም ረድቶት ከልጅነቱ እስከ ዐዋቂነቱ የሰራው ግፍ ወለል ብሎ ታየው። ከዚያ ደግሞ በዚያ ትዕቢቱ የተነሳ እሳቱ የማይጠፋ፣ ትሉ የማያንቀላፋ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ያለበት ሥፍራ ከሞት በኋላ እንደተዘጋጀለት ታወቀውና እንዲህ ብሎ አለቀሰ...
“የወንድሜ ራሱ ጉተናው አማረ
እኔም ባልተሰራኹ ይሻለኝ ነበረ።”
#ማውገዝ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ከልጅነት እስከዕውቀታችን፣ በየሥርዓቱና በየዘመኑ፣ በየምክንያቱና በየሰበቡ፣ ብዙ ሕይወት ሲቀጠፍ፣ ብዙ ደም ሲፈስ፣ ብዙዎች ሲፈናቀሉና ተስፋቸው ሲፈጠፈጥ የዚህን ሁሉ ግፍ ሥረመሰረት አስተውለን፣ እንደ ደላንታው ትዕቢተኛ “ምነው ባልተሰራሁ! ምነው ይህንን ባልሰራሁ? ምነው ይህንን ባላደረግን ብለን ወደራሳችን ጠቁመን፣ የማያዳግም መፍትሔ እንደማምጣት፣ ልክ እንደአባቶቻችን እኛም ጣታችንን ወደሌሎች መቀሰሪያ “ውግዘት” የተባለች ዘመናዊ ከ“ከደሙ ንጹሕ ነኝ” የምንልባት መንገድ ቀይሰናል።

1. ቃሉ ገብቶናል
በመሰረቱ ሊቁ ዐለቃ ደስታ ተክለወልድ “አወገዘ” የሚለውን ቃል ሲፈቱት ፤ “ገዘተ፣ ክፉ ሥራን፣ ክሕደትን ከለከለ፣ ተው አለ ፤ እንቢተኛን ፡ ከሕዝብ አንድነት ፡ ለየ ፡ ወገደ...” ነው ይላሉ። መለየት የምትለዋ ቃል... አንድ ሰው ሌላውን በአንድ ተግባር ለማውገዝ፣ እሱ ከዚያ ሥራ ነፃ መሆኑንና ከ“ደሙ ንፁህ” መሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል። በቀላል አማርኛ አውጋዥ፣ ራሱ ተወጋዥ አለመሆኑን ያውቃል ወይ? ነው።
በዚህ ሁሉ ምስኪን ህዝብ ደም ውስጥ ምንም አላዋጣንም?
በቃልም?
በተግባርም?
በጥላቻ ንግግርም?
ግጭት በማማባስም?
ያልገባን ነገር ውስጥ ተሳትፈን በመፈትፈትም?
በአንድም ይሁን በሌላ፣ በቃልም ሆነ በግብር፣ በማስፈፀምም ሆነ በትብብር፣ ጥፋትን ወደብሔርና ሀይማኖት በመለጠጥና እሳቱን ወደ ሰደድ እሳት በመቀየር... አልተሳተፍንም ወይ?

2. የውግዘት አዙሪት
ግፍ ሲፈፀም... በቅንነት ከሚጮኹት ይልቅ ድምፃቸው ጣሪያ የሚበጥሰው የሟቾችን እምነትና ብሔር እያረጋገጡ የሚጮኹት ናቸው። ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ፀጥ ያሉ መስጊድ ሲቃጠል ድምፃቸው ይጠነክራል፤ መስጊድ ሲቃጠል ጉዳዩን ለማድበስበስ የሚዳክሩት ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ሀገር ካልፈረሰ ይላሉ። ብሔሩም ከሀይማኖቱ ጋር እየተቀየጠና እየተናበበ፣ ሬሳውን እየቆጠረ... ለራሱ በአባላት እና ደጋፊዎቹ መጮህ ማስጮህ... ለሌላው ሲሆን ዝም ጭጭ ማለትን ዓመሉ ካደረገ ከራረመ። ለምን በጋራ አይወገዝም ሲባል... የኔ ሲገደል እሱ ዝም ብሏል፣ የኔ ሲቃጠል የት ነበራችሁ... ይባባላል በየተራ። ይሄ የውግዘት ቅብብል ... የውግዘት አዙሪት ስር ቀረቀረን እንጂ ምን ጠቀመን?

3.ከማውገዝ ጠለቅ ያለ እና ፋይዳ ያለው ሚና የለንም?
ሀገራችን ውስጥ ወንጀልና ቅጥ ያጣ ግፍ የገዛ ወገኖቻችን ላይ ሲፈፀም በየተራ ስናወግዝ ነው የኖርነው።
ምን ጠቀመን? ንፁሃንን አተረፍን ወይስ ለሌላ ዙር ግፍ አመቻቸናቸው? ችግሩን ፈታነው ወይስ አባባስነው?
የድርጊቱ ቀጥተኛ ፈፃሚዎችን ፍርድቤት ዳኛቸው እንበል፣ ችግሩ የተፈጸመበት አስተሳሰብ ከማህበረሰባችን ጠፋልን?
ቅራኔዎቻችን ተፈቱ ወይስ ይብስ እየተለያየን መጣን?
ጉዳዩን የፈፀምነው ወይም ያወገዝነው ከሆነ ብሄር ጥላቻ ከሆነስ... ያ ብሄር ምን ይደረግ?
እናጥፋው?
አንድ ሀይማኖት ላይ ጣታችንን ከቀሰርንስ ያ ሃይማኖት ምን ይደረግ? በሕገመንግስት ይታገድ?
.
.
#ውግዘት ግቡ ግራ የሚያጋባ ድርጊት ነው። ስር የለውም። ንዴትን፣ ጥላቻን፣ እልህን በተቃውሞ ስም የምናወጣበት... እጅም እግርም የሌለው ጊዜያዊ እፎይታ እንጂ እረፍት አይደለም። ስንሮጥ እንታጠቀዋለን ስንሮጥ ይፈታል። ትናትን በሰፈርንበት ግፍ ዛሬ ደሞ እንሰፈራለን። ግን እንደትውልድ፣ የተሻለ ዘላቂ መፍትሔ ማቅረብ አለብን... ይገባናል... ደግሞም እንችላለን!!
.
.

#ማስታወሻ_ለሀይማኖቱ…
ውግዘት እንኳን ፊደል ለቆጠርነው ለሀይማኖት ሰዎችም ዛሬ ላይ አይሰራም። እነሱም የሞራል ስራቸውን በአግባቡ መስራት ትተው በፖለቲካ ድንኳን ውስጥ የሚጋፉ ሆነዋል። እነሱም ቢሆን በአግባቡ የድርሻቸውን ይወጡ። ልብ ማለት ያለብን ዛሬ በሀገራችን የተደገሰውና የሚነገድበት ሞት አንዱና ዋነኛው መጠቅለያው ሀይማኖት መሆኑ ልብ ይሏል።
(እመላለስበታለሁ)