2023-04-11 04:32:50
በዓለም እየኖርን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የመጣው መከራ በአንድም - በሌላ እያገኘን እኔ ከዓለም አይደለሁም በማለት እውነታን መካድ አይገባም ። “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።”
— ዮሐንስ 17፥15
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የሰው ልጆችን ሁሉ ለማዳን ነፍሱን ሲሰጥ በዚህ ዓለም ስርዓት ቢያልፍም ከዓለም ክፉ ሃሳብና የጥፋት ወጥመድ ሳይደባለቅ ለእኛም የማለደው በዓለም እየኖርን እንድንጠበቅና ዓለምን የምናሸንፍበት ጸጋ እንዲበዛልን ነው ።
ከእግዚአብሔር የተወለደ ዓለምን እንደሚያሸንፍ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፤ ከእግዚአብሔር ለመወለድ የመጀመሪያው ተቀዳሚ ተግባር የሰው ድርሻ ኃጢያተኛ መሆኑን አምኖ በራሱ መንገድና የፅድቅ ስራ እንደማይድን ተገንዝቦ ፈጣሪ አምላክ ለሰው ልጆች / ለዓለሙ ሁሉ / በገለጠው መድሃኒት እውነት ፣ ሕይወትና መንገድ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው ።
" ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።
ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? "
1ኛ ዮሐንስ 5 :4 - 5
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ክፋትና ተንኮል በመግለጥ ሰዎች ከወጥመዷ እንዲያመልጡ በማስተማር በፍቅር አሸንፎአል ።
ወድ ወገኖች እኛ እየኖርንባት ስላለችው ዓለም ያለን እውቀት ምን ይመስላል ? ዛሬ ላይ ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ጊዜ ሌላው አህጉር የተከሰተው ችግር የሁሉ እየሆነ በጤና ፣ በኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴያችን አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ በብዙ እየጎዳን ይገኛል ።
አንዳንዶቻችን ተስፋ በመቁረጥ ይህች ጠፊ ዓለም ነች ስለዚህ ዝም ብሎ መኖር ነው በማለት ይባስ ለክፉ የዲያቢሎስ ሃሳብ ተጋልጠው በተሸናፊነት የሚኖሩት ቁጥር ቀላል አይደለም ። እውነቱ ግን ይህ አስተሳሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሰረታዊ አስተምሮ ጋር የሚቃረን ነው ።
እግዚአብሔር ይህችን ዓለም ፈጽሞ ለተወሰነ ስዓት ቢተዋት የሚውጠውን ፈልጎ ዙሪያችንን እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያችንን የሚዞረው ዲያቢሎስን 1ኛ ጴጥ 5 : 8 እንደተገለፀው ሁላችንንም ባጠፋን ነበር ።
እግዚአብሔር ለአንድ ደቂቃ ዓለምና በውስጧ ያለነውን ሕዝብ ፈፅሞ አልጣልም መሰረታዊው እውነት ግን በዓለም ሳለን በመከራ ማለፋችን ግድ ነው ምክኒያቱም የምንኖረው በኃጢያት በወደቀ ዓለም እንደመሆኑ እያንዳንዳችን በግልና በጋራ የምናልፍባቸው አሰቸጋሪ የፈተና ወቅቶች በሕይወታችን ዘመን ይገጥመናል።
በአሁኑ ወቅት ዓለማችን እስከዛሬ ካጋጠሟት በከፋ ሁኔኘታ የኮሮና ቨይረስ በተጓዳኝ ይዞት የሚመጣቸው ችግሮች የከፋ መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኞች በስፋት እየነገሩን ይገኛሉ መጽሐፍ ቅዱስም የመከራው ማብቂያ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ እየጨመረ ይመጣል እንጂ ፈጽሞ ይጠፋል ብሎ አይነግረንም ። ማቴ 24
የመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ 2ኛ ጢሞ 3 : 1 - 5 እንደመሆኑ መጠን የሰዎች ፈርሃ እግዚአብሔር የሌለበት መጥፎ ባህሪ ክሰይጣን ሸንገላና ማታለል ጋር ተደምሮ የዚህችን ዓለም መከራ በይበልጥ አባብሶት ይገኛል ።
በመከራ ወስጥ ለሚያልፈው የሰው ልጅ ማብቂያ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀለትን የከበረ ተስፋ በዚህ ምድር በእምነት ጨብጦ ከዓለም ክፋትና ወጥመድ በማምለጥ በጎ ተጽእኖ እንዲያመጣ ለምድር እንደ ብርሃንና ጨው ጠቃሚ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ።
ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት የምንማረው በተሰጠን ዘመን በዋናነት ለትውልዱ የሕይወትን ቃል በማቅረብ በበጎ ጠቃሚ ስራ የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት ነው ።
" ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች።
በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ ። "
ዮሐ 9 : 4 - 5
በዓለም ውስጥ የመኖሩ ዓላማ የጠፋበት የሰው ልጅ ትክክለኛ ሰው ሆኖ ለተፈጠረለት የከበረ ሕይወት ገብቶት መኖር የሚችለውና ከዘላለም ኩነኔና ፍርድ የሚያመልጠው ፤ አምላክ ከክብሩ ወርዶ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጸንሶ በማርያም ማህፀን በማደር የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በተገለጠው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ነው ።
ሉቃ 1 : 26 - 38
መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከዚህ በኃላ ፍርድ እንደተመደበባቸው ይነግረናል ፤ በመጀመሪያው ሞት ሁሉም የሰው ልጅ ከዚህ ምድር በተለያየ ጊዜ በመጠራት ማለፉ ግድ ነው በርካቶች ወዳጆቻችንም ሆኑ ዘመድ ቤተሰቦች አልፈዋል ነገር ግን ትልቁ የሞት - ሞት በእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ድነት የተሰጠንን መድሃኒት አቅለን ፣ የተፈጠርንበትን ዓላማ ስተን በምድራዊ ሕይወታችን እራሳችንን ሸንግለን በከንቱ ካለፍን ብቻ ነው ።
" በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።
ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም ።
የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው ፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። "
ዮሐ 12 : 46 - 48
በዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ በመዳን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተመራ ለሰው ልጆች ድነት እየማለደ በመፀለይ የምስራቹን የወንጌል ቃል በቃልና በኑሮ በመመስከር ከእግዚአብሔር የተቀበለውን የጸጋ ስጦታና የተፈጥሮ ችሎታ በባለአደራት ትውልድን በመጥቀም በተሰማራበት መስክ እንዲያገለግል ይህ ለሰው ልጆች ሁሉ የተገለጠው የእግዚአብሔር አምላክ ፈቃድ ነው ።
የእኛ ሕይወትና ኑሮ ምን ይመስላል ?
“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።”
2ኛ ቆሮ 13፥14
የጸሎት ጥሪ በዓለማችን ለገጠመን ዘርፋ ብዙ ችግሮች በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ልጆች ድነት የተለያዩ የጸሎት ርዕሶች በመለዋወጥ የሚፀለይበትን የቴሌግራም ቻናል በጸሎት ለመቀላቀል እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማግኘት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ በመጫን መጠቀም በጋራ ማገልገል ይቻላል ።
t.m/harvestministry
24 views01:32