Get Mystery Box with random crypto!

#አጋፋሪ_ይደግሳል ፩ኛ ትርጕም አጋፋሪ፤ አሁን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደረጃ የማኅሌቱን ሥ | ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

#አጋፋሪ_ይደግሳል

፩ኛ ትርጕም አጋፋሪ፤ አሁን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደረጃ የማኅሌቱን ሥርዐት ፥ የዝክር ሁኔታን የሚያስተባብር አጋፋሪ ሲባል፤ ምክትሉ መጨኔ ይባላል
፪ኛ ትርጕሙ፤ አጋፋሪ፤ በቀድሞ ዘመን በሃገራችን በተለይም በቤተ መንግሥት ያለ ሹመት ሲሆን፤ (በጎንደር ፥ በሸዋ ፥ በትግሬ ፥ በወለጋ፥ በአሊባቡር፥ በሐረርጌ፥ በጅማ፥ በወሎ አጋፋሪ ተብሎ ሲጠራ በጎጃም መጨኔ ይባላል/
ሁለቱንም በቀድሞ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው ሁኔታ ትርጕሙን እናያለን ፤

፩ኛ አሁን ካለው የቤ/ክን አገልግሎት አንጻር፤ አጋፋሪ ማለት የማኅሌቱን ሥርዐት ፥ የዝክር ሁኔታን የሚያስተባብር ሲሆን ምክትሉ መጨኔ ይባላል፡፡ ይህ አጋፋሪ በደብረ ታቦር በዓል ላይም በቅዱስ ሚካኤል ተመስሎ፤ ‹‹ሆያ ሆዬ›› ይባላል ይኸውም
‹‹ሆያሆዬሆ››፤ ማለት ጌታው ሆዬ ፥ እሜቴ ሆዬ ለማለት ነው፡፡
‹‹እዚያ ማዶ ጢስ ይጤሳል›› የተባለው፤ እስራኤላውያን በበረሃ ለ40 ዓመታት ሲጓዙ ደመና እየጋረዳቸው (እየጤሰ) ስለመራቸው ነው

‹‹አጋፋሪ ይደግሳል››፤ የተባለው አጋፋሪው /አለቃው/ ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን፤ ይደግሳል መባሉ እስራኤላውያንን ‹‹በዕደ መልአኩ ይዕቀበነ ፥ ሰላመ ዚአሁ የኀበነ›› እንዲል፤ በአምላክ ትዕዛዝ ቅዱስ ሚካኤል መናን ከደመናን ፥ ውኃን ከጭንጫ ዓለት እያፈለቀ (እየደገሰ) መርቷቸዋልና ነው

እንዲሁም የአብነት (የቆሎ) ተማሪዎች በክረምት ሲለምኑ የቆዩትን አጠራቅመው፤ የደብረ ታቦር ዕለት ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ ለኛም እንዲገልጥልን ብለው፤ ደግሰው ለሕዝቡ ያበላሉ ፥ ያጠጣሉ፡፡ /ይህ ሥርዐት በደብራችንም የሚከናወን ድርጊት ነው፡፡/
‹‹ያችን ድግስ ውጬ ውጬ››፤ የተባለውና በድግስ የተመሰለው መና ሲሆን፤ በደጋሹ ቅዱስ ሚካኤል አማካይነት እስራኤል 40 ዓመታት መመገባቸውን (መና መዋጣቸውን) መናገር ነው፡፡

‹‹ከድንክ አልጋተገልብጬ›› ፤ ድንክ አልጋ የምትመች እንደሆነች ሁሉ ፥ በድንክ የምትመሰለውንና የምትመቻቸውን ተስፋዪቱ ምድር ኢየሩሳሌምን መውረሳቸው መናገር ነው

‹‹ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ፥ ያለ አንድ ሰው አታስተኛ››፤ መባሉ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ 600,000 ሆነው ሲሆን፤ ሁሉም በምድረ በዳ አልቀው ኢየሩሳሌምን የወረሳት ሴትና ሕፃናት ሳይቈጠሩ፤ አንድ ኢያሱና አንድ ካሌብ ናቸው ለማለት ነው

፪ኛ አጋፈረ፤ግስ ሲሆን በቤተ መንግሥት ፥ በግብዣ ቦታ፥ …. በር ላይ ቆሞ የሚገባውንና የሚወጣውን ሰው አስተናበረ አስተናገደ አጋፋሪ፤ ቅጽል ሲሆን፤ ቃሉ የቀድሞ አማርኛ ሲሆን አስተናባሪ (ብዙውን ጊዜ በግብዣ ወይም በቤተ መንግሥት በር ላይ በመቆም ሥርዐት የሚያስከብር ማለት ነው

አጋፋሪ፤ የድግስ አለቃ ፥ አስተናጋጅ ነገሥታት ግብር ሲያገቡ (ግብዣ ሲጋብዙ ፥ ድግስ ሲደግሱ) ወደ አዳራሹ (ወደ ድግሱ) እንዲገቡ የሚፈቅድ ፥ የማይገባቸውንም የሚከለክል፤ ከገቡም በኋላ እንደ የክብራቸውና እንደየማዕርጋቸው አንተ በዚህ ሁን ፥ አንተ በዚህ ተቀመጥ እያለ የሚያስቀምጥ፤ ኋላ የድግሱ ምግብና መጠጥ መታደል ሲጀምርም፤ እንጀራና ጠጅ አሳላፊዎችን የሚያዝና የሚቈጣጠር ትልቅ ሹም ነው

አጋፋሪ፤ የሚለው መጠሪያ በ17ኛወና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀ የቤተ መንግሥት ሹም መጠሪያ ነው፡፡ ‹‹ህዱግ ራስ›› በመባል የሚታወቅም ነው፤ በቤተመንግሥት የሚካሄዱ ሥራዎችንና የፍርድ ሂደቶች ያስተባብራል፤ አንዳንዴ ደግሞ የክፍላተ ሃገር የፍርድ ሰጪ ሰዎች ስም ሆኖም ያገለግላል፤ የስሜን (ከጎንደር በስተሰሜን የሚገኝ ግዛት ነው) አስተዳደር የሚገዛ ሰው ደግሞ የሰሜን አጋፋሪ እየተባለም ይጠራል፤ (ለምሳሌም አፄ ሱስንዮስ ልጃቸውን ፋሲለደስን የስሜን አጋፋሪ ብለው ሹመወት ነበር፤ ይህ የስሜን አጋፋሪ የሚለው ሹመትም እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቆይቶ ነበር፡፡

ቡሄ
ቡሄ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጸበት የነሐሴ 13 ቀን መጠሪያ ስሙ ነው የሚሉ ሊቃውንት እንዳሉ ሁሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ቡሄ የሚባለው፤ ከነሐሴ 13 በኋላ እስከ መስከረም 17 መስቀል ድረስ ሲሆን፤ በተለይም ይህ በዓል የሚታወቀው በሸዋና ወሎ /እስከ ጋይንት ጫፍ መጋጠሚያ) ድረስ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም ክርስትና አባት ለክርስትና ልጁ ተማሪ ከሆነ መጻሕፍትን (ዳዊት፣ …)፣ እንዲሁም አልባሳትን፣ በግና ሙክት ፍየልን የሚሰጥበት ነው፡፡ ሕፃናትና ወጣቱም ‹‹ቡሄ ፥ ሆ ….. ›› እያለ ይጨፍራል ፤ የሚሰጠውንም ሙክትና በግ እስከ መሰቅል ድረስ ሲያጠራቅም ከርሞ ለመስቀል ዕለት አርዶ ይበላል ፥ ደስታን ያደርጋል

ምንጭ፤ የቃል ትምህርት
/የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰ/ት/ቤት/

@finotebrhan
@finotebrhan
@finotebrhan