Get Mystery Box with random crypto!

#ሆሳዕና ሆሳዕና በእብራይስጥ 'አሁን አድን' በግዕዝ ደግም 'መድኃኒት' ማለት ነው። ሆሳዕና | ፍኖተ ኦርቶዶክስ

#ሆሳዕና

ሆሳዕና በእብራይስጥ 'አሁን አድን' በግዕዝ ደግም 'መድኃኒት' ማለት ነው።

ሆሳዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።

ሆሳዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ለምን ከረቡዕ ጀምሮ ይታሰባል ቢሉ ጌታችን ሐዋርያትን አህያይቱንና ውርንጫዋን ያመጡ ዘንድ ወደ ቤተፋጌ እንዲሄዱ ያዘዛቸው ረቡዕ ነው እነሱም ፈልገው ያመጧቸው በዕለተ እሁድ ነው።

በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ "ሆሳዕና በአርያም" "ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት" "ዕለተ ሆሳዕናሁ አርዓየ… " ወዘተ... በማለት እየተጠቀሰና እየተዘመረ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበት ሁኔታ እየተተረከረ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሳዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።

በአህያ መቀመጡ፦
1, ትህትናን ለማስተማር።
2, የሰላም ዘመን ነው ሲል(በብሉይ ዘመን ነቢያት የክፋት ዘመን መምጣቱን ሲናገሩ በፈረስ ላይ ተጭነው ይታያሉ፤ የሰላም ዘመን የምህረት ዘመን መምጣቱን ለማሳየት በአህያ ላይ ይቀመጣሉ።)
3, በአህያ ላይ የተቀመጠ ሰው ሮጦ አያመልጥም ክርስቶስም ከፈለጋችሁኝ እገኛለሁ ሲል በአህያ ላይ ተቀምጧል ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል በንጽህና በየዋህነት ለሚኖሩ ምዕመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል ነው፡፡

ለምን ዘንባባ ያዙ ቢባል፦ ዘንባባ እሾሃም ነው፤ አንተም የኃይል የድል ምልክት አለህ ሲሉ፤ በሌላም በኩል ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተም ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ፤ አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡

የተምር ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፦
ተምር ፍሬው አንድ ነው አንተም ባህርይህ አንድ ነው ሲሉ፡፡ አንድም፤ ተምር ልዑል/ረጅም/ ነው አነተም ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ፡፡ አንድም፤የተምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው በቀላሉ መልቀም አይቻልም ፤ የአንተም ምስጢር አነተ ካልገለጠከው አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡

የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፦
ወይራ ጽኑዕ/ ጠንካራ/ ነው አንተም ጽኑዓ ባህርይ ነህ ሲሉ፤ አንድም ወይራ ለመስዋዕት ይሆናል፤ አንተም መስዋዕት ትሆናለህ ሲሉ፤ አንድም ወይራ ዘይቱ ለመብራት ይሆናል አንተም የዓለም ብርሃን ነህ ሲሉ ይህንን ይዘው አያመሰገኑ ተቀበሉት፡፡

ልብሳቸውንም ማንጠፋቸው፦
እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ እንኳን መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉለት፡፡ እነዚያ ያላመኑ አይሁድ ለተቀመጠባት አህያ ይህንን ያህል ክብር ከሰጡ፤ በድንግልና ጸንሳ ለወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምን ያህል ክብር ልናድረግለት ይገባን ይሆን?

ዲያቆን ቃለአብ ግርማ