Get Mystery Box with random crypto!

' ለሁሉ ጊዜ አለው”መክ 3፥1 የሰው ልጅ በሕይወቱ አራት ዘመናትን ያሳልፋል የመጀመርያው | ትምህርተ አበው

" ለሁሉ ጊዜ አለው”መክ 3፥1

የሰው ልጅ በሕይወቱ አራት ዘመናትን ያሳልፋል የመጀመርያው ዘመነ ነፋስ ሲሰኝ ይሄውም የህጻንነት ዘመን ነው ሁለተኛው ዘመነ እሳት ሲሆን ይሄውም የወጣትነት የማዕከላዊነት የዕድሜው ክፍል ነው ሦስተኛው የውሃነት ዘመን ሲሆን ይህም የጎልማሳነታችን ወቅት ነው የመጨረሻው የመሬትነት ዘመን ሲሆን ይሄም ወደ ምድር የምንመለስበት ነው ታድያ እነዚህ ዘመናት የሚፈራረቁት ግዜያቸውን ጠብቀው በጊዜያቸው ነው ወዳጄ ዳዴ ሳይል የቆመ የለም ለሁሉም ጊዜ አለው።

በምድር የምናያቸውን ፍጥረታት እግዚአብሔር ለመፍጠር 6ቀን ፈጅቶበታል ይህን ስታስብ ምን ይሰማሃል? ሁሉን ከዓይን ጥቅሻ ፈጥኖ መከወን የሚቻለው ጊዜ የማይወስነው የጊዜ ባለቤት እግዚአብሔ 22 ሥነ ፍጥረታትን በ6 ቀን ፈጠረ?ወዳጄ በቅጽበት ማድረግ የማይሳነው አምላክ እንዲህ ያደረገው የጊዜን ምንነት ሲያስረዳ ነው እንደውም ሊቃውንት የሙሴን ቃል ይዘው ሲያመሰጥሩ ቀዳሚው ፍጥረት ጊዜ እና ሥራ ነው ይላሉ"በቀዳሚ እግዚኣብሔር ግብረ ሰማየ ወምድረ" ዘፍ 1፥1

በሕይወት ማድረግ የሚገባህን በጊዜው አድርግ ከጊዜህ ቀድመህም ዘግይተህም አትገኝ ሁሉን በጊዜህ አድርግ ጊዜህንም በአግባብ ተጠቀም ከወተቱ አጥንቱን አታስቀድም በወጣትነትህ ምርኩዝ ለመያዝ አትመኝ ሁሉን ማድረግ በሚገባህ ጊዜ አድርግ ነገ እንዳትቆጭ ዛሬ በእድሜህ መስራት ያለብህን ሰርተህ እልፍ ነገ እንዳትፀፀት ዛሬ መስራት ከማይገባህ ግብር ራቅ።


የምታስበው ሁሉ ባይሆንልህ ተስፋ አትቁረጥ ይህንን አስብ "ለሁሉም ጊዜ አለው" እግዚኣብሔር የሚመጣበት ጊዜው ዛሬ ላይሆን ይችላል አንተ እንዲኖርህ የምትመኛቸውን ነገሮች ሲኖሩህ ምን ማድረግ እንዳለብህ አስብ በጊዜህ የምትሰራውን ብቻ ሥራ አንተ ድርሻህን ከተወጣህ ነገሮችን መፈጸም የፈጣሪ ድርሻ ነውና የእርሱን ጊዜም ጠብቅ።

ጊዜህን በአግባብ ተጠቀም ሁሉ ዛሬ ካልሆነ አትበል የዛሬን አድርገህ በትላንት ትዝታ በነገ ተስፋ ትኖራለህን የአንተ ስጦታ ዛሬ ናት ዛሬ ማድረግ የሚገባህን ብቻ አድርግ ምናልባት ነገ ላትኖር ትችላለህ ብትኖርም የነገውን ነገ ትደርስበታለህ ብቻ ዛሬ የምታስቀምጠው ዛሬ የምትሰራው ነገ የምትፀፀትበት እንዳይሆን ለማድረግ ጣር።

አታርፍድም አትቸኩልም
“ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።”
መክብብ 3፥1


ግንቦት 30/2014ዓ.ም
ዲ/ን ፍቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)