Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለእግዝእትነ ማርያም (#በዓታ): አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ እና ቅዱስ ፋኑኤል ዓመታ | የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት መዝሙር እና ኪነ-ጥበብ ክፍል(የፈ/ጥ/ሰ/ት/ቤት ደብረ ዘይት)

††† እንኳን ለእግዝእትነ ማርያም (#በዓታ): አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ እና ቅዱስ ፋኑኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም †††

††† ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ::
እርሱ:-
*ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ:-
*የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)

††† "ለጽንሰትኪ በከርሥ::
እንበለ አበሳ ወርኩስ::
ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. 1:9)
"ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ::
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::"
"ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን::
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን)"

የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::

ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::

እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች:: ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)

††† የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:-
ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::

*በአባቷ በኩል:-
ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::

ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,023 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለ3 ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ: ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ:: በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም::

ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር:: 3 ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ::

እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ:: ሕዝቡ: ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን: ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ::

ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ:: ግን መልአኩ ራቀ:: ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ: ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት:: በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል::

አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ:-
"ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ::
ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ::
ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ" እንላለን:: (አርኬ)

††† አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ †††

††† አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው:: ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል:: ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ-የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል" (መዝ. 111) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል::

ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ:: ስማቸው ጸጋ ዘአብ: እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል:: ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ: እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለ ሃይማኖትን ሲወልድ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል::

የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ 30 በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር 24 ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው:: ዘመኑም 13ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::

ዜና ማርቆስ በተወለዱ በ40 ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የ72 ዓመት ሽማግሌ ናቸው) ሊያጠምቁ ቀረቡ:: ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው 3 ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ::

ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ" አላቸው:: እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው::

ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን 5 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው: በትራቸውን ቀምተው: አንገላተው ሰደዋቸዋል::