Get Mystery Box with random crypto!

ሆሣዕና ምን ማለት ነው? የወይራ ዛፍና የዘንባባ ዝንጣፊ ምስጢራዊ ትርጓሜ ምንድነው ? ጌታ በአ | "ልጆቼ የቤተክርስቲያንን ነገር አደራ"

ሆሣዕና ምን ማለት ነው? የወይራ ዛፍና የዘንባባ ዝንጣፊ ምስጢራዊ ትርጓሜ ምንድነው ?
ጌታ በአህያ የመቀመጡን ምክንያቱን ለማወቅ

= ሆሣዕና ማለት መድኀኒት ማለት ነው
ሆሣዕና የጌታችን የአምላካችን በዓል ነው
ከጌታችን ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው።

✥ ሆሳዕና ክፍል 1✥

በዕለተ ሆሳዕና እስራኤላውያን ለምን የዘንባባ ዝንጣፊ ፤ የቴምር ዛፍ ዝንጣፊ እና የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ዘመሩ? (ማቴ. 21÷1-17፣ ማር. 11÷ 1-10፣ ሉቃ. 19÷29-38፣ ዮሐ. 12÷12-15

የዘንባባ ዝንጣፊ፡-
☞ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ አብርሃም ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሄርን አመስግኖበታል የደስታ መግለጫ በመሆኑ አነተ ደሰታ የምታስገኝ ሃዘናችንንም የምታርቅ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
☞ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ህይወት ይዘራል የደረቀ ሕይወታችንን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው
☞ ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው የሰላም አምልክ ነህ ሲሉ ነው
☞ ዘንባባ እሾሃማ ነው አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው
☞ ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጅ ጌታም አንተ ባህርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው
☞ ዘንባባ የነፃነት ምልክት ነው ከባርነት ነፃ የምታወጣን አንተነህ ሲሉ ነው አኛም ይህን በማሰብ ዘንባባ ይዘን ሆሳእና በአርያም እያልን እለቱን እናስባለን፡፡

የቴምር ዛፍ ዝንጣፊ፡-
☞ የቴምር ዛፍ ፍሬ ጣፋጭ ነው፦ በሃጥያት የመረረውን ሂወታችን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
☞ የቴምር ፍሬ የሚገኘው ከዛፉ ከፍታ ላይ ነው አንተ አምላካችን ልዑለ ባህሪ ነህ ከፍ ከፍ ያልክ አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
☞ የቴምር ዛፍ ፍሬ በውስጡ ያለው ፍሬ አንድ ነው አንድ አካል አንድ ባህሪ ነህ ሲሉ ነው።
☞ የቴምር ፍሬ በእሾህ የተከበበ ነው ይህም የአንት ባህሪ የማይመረመር በእሳት የተከበበ ነው ሲሉ ነው።

የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ፡-
☞ የወይራ ቅጠል የሰላም ማብሰሪያ ነው ሰላማችንን የምታበስርልን የምታስገኝልን አንተ ነህ ሲሉ ነው፡፡
☞ የወይራ ቅጠል ከእንጨት ሁሉ ጽኑ ነው አንተም ጽኑ ሃያል አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
☞ ወይራ ለመብራት ያገለግላል ፍሬው ዘይት ያወጣል ከወይራ የሚገኝ ዘይት ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ አንተም ጨለማ ህይወታችንን የምታስወግድልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
☞ በኦሪት ግዜ የወይራ ዘይት ለመስዋአትነት ይቀርብ ነበር አንተም እንደ ዘይቱ ለመተላለፋችን መስዋዕት ሆነህ የምትቀርብ አምላክ ነህ ሲሉ ነው። በመስቀል ላይ መስዋዕት ሆኗልና።

❖ ጌታችን አምላካችን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ፊታችው ባለው ሀገር ሂዱና አህያ ከውርጭላዋ ጋራ ታስራ ታገኛላችው ፈታችው እምጡልኝ ምን ታደርጋላችው? የሚላቸው ሰው ካለ ጌታቸው ይፈልጋቸዋል በሉ ብሎ ላካቸው

ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዳዘዛቸው ሂደው ፈተው አመጡለት
በዚያም የተሰበሰቡት ሁሉ በአህዮች ላይ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት ጌታችንም በሁለቱ አህዮች ላይ ተቀመጠ

ከሌሎቹ እንስሳት አህዮችን መርጦ በአህዮች ተቀምጧል
አህዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪክ አላቸውና።

❖የበልአም አህያ የመልአኩን ክብር ለመግለጥ አፍ አውጥታ ተናግራለች ዘሁል22÷28

❖ ጌታችን በተወለደ ጊዜ አህዮች ከከብቶች ጋር
በበረት እስትፋሳቸውን አሟሙቀውታል ቅዳሴ ማርያም

❖ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ለመግጽ

ምሳሌ- ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብእ ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ ዘመነ ሰላም ከሆነ
በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበርና ጌታችንም ዘመነ ሰላም ነው ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።

❖ ትንቢቱን ለመፈጸም
ትንቢት- አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው
ትሁትም ሁኖ በእህያም በውርንጭላቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል ብሎ ዘካርያስ ትንቢት ተናግሮ ነበርና ለመፈጸም ነው ዘካ 9÷1

❖ምሥጢሩን ለመግለጽ
ምሥጢር- በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጋችሁኝ አልገኝም ከፈለጋችሁኝ አልታጣም ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል ይህ እና ሌሎች ምስጢራትን ለመግለፅ ትንቢት ለመፈጸም አምላካችን በአህ።

❖ በዓለ በሆሳዕና ጊዜ የጌታችን ትህትና የምናስብበት እኔ ምሰሉ ስላለ በትህትና እራሳችንን የምናኖርበት ። በእላይ በሰማይ ኪሩቤል በፍርሃት መንበሩን የሚሸከሙት ቅዱሳን መላእክት ያለማቋረጥ የሚመሰግኑት በትህትና በአህያ ጀርባ የተቀመጠ በሕፃናት አንደበት የተመሰገን ቢታንያ ድንጋዮች የዘመሩለት የአምላካችን የጌታችን ክብረ በዓል በምናከብረበት ጊዜ የአምላካችን ትህትናውን በልባችን እያሰብ በተግባር እየገለጥ እንድንኖር አምላካችን ይርዳን ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
ይቆየን