2022-06-20 11:04:00
በአዲስ ችቦ፣ በአዲስ ጮራ፣ የምታብብ እንደገና።
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ቤዛ፣ እናት ፀሐይ እናት ሰላም፣
ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ናት፣ የአፍሪካ ዘለዓለም ገዳም፣
ያጠፋትን እያጠፋች፣ ታበራለች እንጂ አትጠፋም።
ኢትዮጵያ ዘለዓለም ሰላም፣ ዘላለም ፀሐይ ብሥራት፣
ለዓለም ሥልጣኔ ቁንጮ፣ ለዓለም የጥቁር ዘር ኩራት፣
ለወዳጆቿ ብርሃን፣ ለጠላቶቿ ግን እሳት፣
“እጆቿን ወደ እግዚአብሔር፣” ዛሬም “እንደ ዘረጋች” ናት።
ብሩህ እንጂ ምጡቅ ጥበብ፣ ኢትዮጵያዊነት መች በእልክ፣
የሚካኑበት ቅጥፈት ነው፣ በዘረኝነት ንትርክ?'
የኢትዮጵያዊነት ጥበቡ፣
መደናበር ሳይሆን ግቡ፣
በሆድ አምላክ ከመታወር፣
በደም ጭቃ ከመነከር፣
ለንቅዘት ጣኦት ከመስገድ፣ ተፈቃቅዶ በመከበር።
መቻቻል ነው በአገር ሕብረት፣
በአርቆ ማስተዋል ምሥጢር፣ አንድነት በካበተበት፣
ለነገው ትውልድ ተስፋ፣ አዲስ ጎህ እንዲታይበት፣
የልዕልና መክሊት ነው፣ ራዕይ ነው ኢትዮጵያዊነት።
ስማችን ዛሬ ቢበዛም፣
ማሞካሻችን ቢንዛዛም።
አንዳንዴ “በነፍጠኝነት፣” አንዳንዴም “በውሾች” ጩኸት፣
አንዳንዴም “በሃድጊ” ጭነት፣ አንዳንዴም “በጨርቅ” ዝትት፣
መንፈሳችንን ለማቁሰል፣ ያለለከት ብንጠራም፣
ኢትዮጵያዊነት ርቱዕ ነው፣ በነቀዝ አፍ አይፈታም።
ምክንያቱም ከመሠረቱ፣ በኢትዮጵያዊነት እምነቱ፣
ሕዝብን ነፃ ማውጣትና፣ ነፃነት መንጠቅ ዓይነቱ፣
የተለየ ነው ሥርዓቱ።
ለሕዝብ ነፃነት ገድል፣ ሕይወቱን መስዋዕት አርጎ፣
እንደገና ነፃነቱን ከሕዝቡ እጅ ሰንጎ፣
በጠመንጃ ጉልበት ነጥቆ፣ የዓለም ዴሞክራሲን ሸማ፣
የሃፍረት ማቅ አከናንቦ፣ የኢትዮጵያዊነቱን አርማ፣
በአንድ አናሣ ጎሣ ቡድን፣ በዘረኝነት ግፍ አድማ፣
በአደባባይ እያደማ፣ ነፃ አውጪ ነኝ ማለት ደሞ፣
ለዕብሪተኝነት ነው እንጅ፣ መቼ ለነፃነት ቆሞ?!
ኢትዮጵያዊነት ምጡቅ ነው፣ ለዕኩይ ሥንዝር አይሟላም፣
በጠባብ ክንድ አይለካም፣
የዘረኝነት መቅነት፣ ለሽንጧ ቁመት አይበቃም።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት፣ አስቀድሞ ራስን አውቆ፣
የካም አበው መነሻውን፣ ማንነቱንም ጠንቅቆ፣
በአንድ እናት አገር ልጅነት፣ የሕብረት ሸማ ተላብሶ፣
በዓለም ሥልጣኔ መሥራች፣ ሳይንሳዊነት ምሰሶ፣
በሥልጣኔአችን ታሪክ፣ ከፅንፍ ፅንፍ ታድሶ፣
እያስተጋቡ በርቱዕ፣ ለነገው ትውልድ ሰንደቅ፣
“ከሕዝብ ለሕዝብ በሕዝብ፣” ዴሞክራሲን ማንፀባረቅ፣
ነውና ኢትዮጵያዊነት፣ “ጥቁር-እሳት-ፀሐይ ሰላም”
ኢትዮጵያ የካም ግንድ እናት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ገዳም
ያጠፋትን እያጠፋች፣ ታበራለች እንጂ አትጠፋም።
ጥራቱ እንደ ምንጭ ውሀ፣ ድብብቆሽ ያልከለለው፣
ብሩህ እንደ ሜሮን ፀበል፣ ኢትዮጵያዊነት ግልፅ ነው።
ይኼ ተለጉሞ መዳህ፣ ተጭቁኖ “መረጋጋት”፣
አጎብድዶ ለአምባገነን፣ እንደ መጋጃ መነዳት፣
ኢትዮጵያዊነት አደለም፤
ይኸ ፈርጥጦ ሩቅ ሆኖ፣ ከስደት ኬላ ማላገጥ፣
ከሕዝብ ሰቆቃ ሸሽቶ፣ ኢትዮጵያን በጣር ማፋጠጥ፣
ጽዋዉን አብረው ሳይቀምሱ፣ ትውልዱን ከሞት ማጋፈጥ፣
ራስን ከሃቅ ደብቆ፣ በስደት ዋሻ ማሽቃበጥ፣
ነገ በሥልጣን ኮርቻ፣ እንደ ታቦት ለመቀመጥ፣
ቀቢፀ ተስፋን ማቁነጥነጥ፣
ኢትዮጵያዊነት አደለም፤
ይኸ በቁም ተደናብሮ፣ በመገነጣጠል ሮሮ፣
ጤና እንደሌለው አእምሮ፣ በጎሠኝነት ተሳክሮ፣
ወደ ሲኦል መሽቀዳደም፣ በዘር ጥላቻ ታውሮ፣
ኢትዮጵያዊነት አደለም፤
ይኸ በቅዠት ተናውጦ፣ ማስረከብ ሰብአዊ ክብርን፣
እንደ አጋሠሥ መኮርኮዳ፣ ያው ሳይንተራሱ ክንድን፣
ኢትዮጵያዊነት አደለም፤
ግን ያለ ውድ በግዳጅ፣ ተገፍትሮ ለባርነት
እምቢኝ ማለት ለነፃነት።
ከኢትዮጵያዊነት ዓላማ ፣ በየጎጥ ሳንዘናጋ፣
ለእኩልነት መዋደቁ፣ ፅዋን መቀበል በፀጋ፣
የመንፈስ ኩራት አብነት፣ የማይተመን በዋጋ፣
አበው በደም ያወረሱን፣ ዓፀመ ርስት ነው የዜጋ።
በጎሠኝነት ትምክህት፣ ጀርባውን ጎጡ ያልቀደደው፣
አንድነታችን ከብረት፣ እንዲጠነክር እንደ አበው፣
በኢትዮጵያዊ ማተባችን፣ እንድንተምም እንደ ንብ፣
ደማችን የኢትዮጵያ ልብ፣ ግባችን የሕዝባችን ግብ፣
አገራችን ሰንደቃችን፣ ዜጋችን የኢትዮጵያ ሕዝብ
ሲሆን ብቻ ነው ዘለዓለም፣ ኢትዮጵያዊነት እሚያብብ።
240 views08:04