Get Mystery Box with random crypto!

Dawit Kebede የብርሃን እናት ! ባልተለመደ መልኩ በዕንባ ብዕር የተጻፈን የብርሃን እናት የ | EOTC Books የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. መጻሕፍት

Dawit Kebede
የብርሃን እናት !
ባልተለመደ መልኩ በዕንባ ብዕር የተጻፈን የብርሃን እናት የተሰኘ መጽሐፍ በልብ ሥቃይ አንብቤ ከተፈወስኩ በኋላ በተለመደ መልኩ በገጽ ብዛቱ ፣ በምዕራፉ እና በሥነ ጹሐፍ ውበቱ መጀመር የበሽተኛ ሐኪም ፣ የወንጀለኛ ዳኛ ፣ ቀበጥ ቁስለኛ ስላደረገኝ ዐይኑ የበራለት ኹሉን ትቶ ማየት በመቻሉ የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ እንደሚቸኩል ኹሉ "መቼም ልብን አኮማትሮ ደስ ይበልህ ማለት የለምና " የልቤን ደስታ ብቻ ለመግለጽ ቸኮልኩ !
ሄሮድስ ጌታን ብቻ ያሳደደ መስሎት እናቱን ጭምር ስደተኛ አድርጎ ነበር ። ዛሬም እናቱን ብቻ ያሳደዱ መስሏቸው ጌታንም ጭምር ከእስራኤል ልባቸው ላሳደዱ ኹሉ ይህ የብርሃን እናት መጽሐፍ ዳግማዊው ሄሮድስን ከልባቸው ገድሎ "የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ዳግማዊ ሄሮድሶች ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል ልብህ ተመለስ" የሚያሰኝ ይመስለኛል ።
አዳምና ሔዋን ሆይ ከዚህ ቀደም ያለመታዝ ቁስላችሁን አመጣጥ አጥብቆ መርማሪ ባለመኖሩ ለአንዳዶቻችን እስካሁንም መድኃኒት ያልተገኛችሁ በሽተኞች ፤ ለሌሎቻችን መድኃኒት ያላስፈልጋችሁ ጤነኞች ለብዙዎቻችን ደግሞ ብቸኛ በሽተኞች ነበራችሁ ዛሬ ግን የእናንተንም የኛንም በሽታ ከነመድኃኒቱ አጥብቆ መርማሪ የብርሃን እናት አግኝታችኋልና ደስ ይበላችሁ !
የብርሃን እናትን የሚያነብ ኹሉ ቅዱስ ባስልዮስ ሐኪም እነደመሆኑ ስለ ሰው ልጅ የመጀመሪያ ያለመታዘዝ በሽታ ሲተነትን ፤ ቅዱስ ኤፍሬም እና ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ደግሞ ከበሽታው ይልቅ ስለ መድኃኒቱ ሲራቀቁ ያገኛቸዋል ። ከኹሉ ይልቅ እኔን የደነቀኝ ግን የበሽታውም የመድኃኒቱም ጠቢብ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጉዳይ ነው ! ይህ አባት የብርሃን እናት ታማኝ ምስክሯ ነውና በዚህ መጽሐፍም ትውልድ ኹሉ ከእርሱ ጋር እንዲተዋወቅ የብርሃን እናት ለወዳጇ ሄኖክ አደራ ያለችው ይመስለኛል !
አንዳንድ ጊዜ ትጉህ ፣ የበሽታ መንስኤን ጠንቅቆ አዋቂ እና መርማሪ ባለ መድኃኒት ሲገኝ ከዚህ ቀደም ለአንድ በሽታ ብቻ ሲውል የነበረ መድኃኒት የሌላ ዘመን አመጣሽ ደዌ አስተማማኝ መፍትሔ ሆኖ እንደሚገኝ ኸሉ በብርሃን እናት ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ከዚህ በፊት ከምናውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ መድኃኒት ጥቅሶች ውስጥ ከዚህ ቀደም ለመድኃኒትነት ያልዋሉ እና ለአንድ በሽታ ብቻ ሲውሉ የነበሩትን መድኃኒቶች ለአያሌ የዘመናችን በሽታዎች መፍትሔ እንዲሆኑ ያደረገ ብልህ ባለመድኃኒት መሆኑን የምትረዱት መጽሐፍን እንደኔ ስታነቡ ብቻ ነው !
ሌላው ያስደነቀኝ ነገር ጸሐፊው ለሚያነሳቸው ሃሳቦች በሙሉ ነቢያቱም ፣ ሃዋርያቱም ፣ ቅዱሳኑም ተሽቀዳድመው "እኔ ምስክር ልሁንህ ! እኔ ምስክር ልሁንህ !" ብለው የተረባረቡበት መንገድ ነው ። ይህን ላስተዋለ ዲያቆን ሄኖክ "እናንተ ብቻ የቅዱሳን ወዳጅ ኹኑ እንጂ ያለ ምስክር ብቻችሁን ላለመቅረታችሁ የብርሃን እናት ኀያው ምስክሬ ናት ! " እያለን ይመስለኛል !
ጌታ መድኃኛችን የሆነው ሕማሙ ምስክር ለሆነው ለቅዱስ ዮሐንስ በምድር ላይ የቀረች አንዲት ሀብቱን እናቱን ከመስቀሉ ሥር እንደሰጠው ይታወቃል። ቢሰጥ የማያልቅበት ነውና ዛሬም በየዘመናቱ የሕማሙ ምስክር ለሆኑትም እናቱን እንካችሁ ብሎ ይሰጣቸዋል። ሕማማት በተሰኘው መጽሐፉ ልባችንን ወደ ቀራኒዮ ለወሰደው የቁስሉ ምስክር ሄኖክም " እናትህ እነኋት" ብሎት የብርሃን እናትን ወደ ቤቱ ወሰዳት.....መልካም ንባብ
ዲ/ን ዶ/ር ዳዊት ከበደ
የካቲት 18 2014 ዓ.ም