2023-06-15 16:10:07
በአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባለፉት 11 ወራት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል
********************************
የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በአዲስ አበባ ኤርፖርት የሚታየውን የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድ ዝውውርን ለመግታት የሚያስችል ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ መኮነን ፤ የአዲስ አበባ ኤርፖርት በርካታ ዓለም ዓቀፍ መንገዶችን የሚያስተናግድ ከመሆኑ የተነሳ የኮንትሮባንድ ፍሰቱ በየጊዜው እየጨመረ እና ውስብሰብ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት የበጀት ዓመት 11 ወራት ብቻ 152 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የወጭና 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ፤ በድምሩ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ኤሌክትሮኒክስ፣ አደንዛዥ እፆች ፣ የጦር መሳሪያ ፣ ማዕድናት ፣ የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች ፣ መድኃኒቶች ፣ አዝዕርትና የዝሆን ጥርስ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱም አቶ ተፈሪ አብራርተዋል ::
በጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ በበኩላቸው፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በመከላከልና በመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱን የሀገር ደህንነት ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ወንጀልን መከላከል እና መቆጣጠር ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ብሎም መላው ህብረተሰብ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የኮንትሮባንድ ዝውውር በሃገር ሰላም ፣ በህዝብ ደህንነት እና በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጉዳት ለመከላከል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸውም የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/ecczena
በድረ ገጽ፦ www.ecc.gov.et
በቴሌግራም፦ https://t.me/EthiopiaCustomsCommission
1.8K viewsYonas Damtew, 13:10