Get Mystery Box with random crypto!

#ወራቤ_ላይ_ሌላ_ትኩሳት ================= የወራቤ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን መግለጫ አነበብ | Ethiomedia

#ወራቤ_ላይ_ሌላ_ትኩሳት
=================
የወራቤ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን መግለጫ አነበብኩት ይዘቱ ትውልድ ከሚገነባና የእውቀት ማዕከል ከሆነ የፌደራል ዩኒቨርስቲ የመነጨ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል? ከዚህ በላይ ደግሞ ዩኒቨርስቲው የሃሳብ ማንሸራሸርያ፣ የእውቀት መሰረት፣ የፍትሐዊነትና የትውልድ ግንባታ ተቋም መሆኑ ቀርቶ የዛቻ፣ የማስፈራሪያና የእገታ ተቋም መሆኑ ይበልጥ አስደንጋጭ ሆኖብኛል?!

የወራቤ ዩኒቨርስቲ በአደራ የተረከባቸውን ተማሪዎች በመግለጫ ምርኮኛ ሲያደርጎቸውና ለጥቃት አሳልፎ ሲሰጣቸው ትምህርት ሚኒስቴር ከወዴት አለሁ እያለ እንደሆነም ሊገለጽልኝ አልቻለም !! ክልሎችስ በአደራ ለዩኒቨርስቲዎች የሰጧቸው ልጆቻችን ሳይሸማቀቁና ሳይፈሩ ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ምን ጥረት እያደረጉ ነው የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል? ክልሎች ልጆቻችንን በፍላጎታቸው መሰረት ትምህርት አቋርጠው በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ምን እያደረጋችሁ ነው?! ልጆቻችን ከሞታቸው አሟሟታቸው እንዳይሆን ምን ከለላ አላቸው?! ነግ በኔ ነውና እጠይቃለሁ?!

ለመግቢያዪ ምክንያት የሆነኝን የወራቤ ዮኒቨርስቲ መግለጫን ዝርዝሩን ትቼ በሁለት ጉዳዮች ላይ ብቻ በአደራ ልጆቻችንን የሰጣችሁ ክልሎችን ልጠይቅ ?!

አንደኛ

የወራቤ ዮኒቨርስቲ መግለጫ "ነገር ግን" ይላል "ያለ ዩኒቨርስቲው ፍቃድ ትምህርታችሁን አቋርጣችሁ የምትሄዱ ተማሪዎች "ለሚያጋጥማችሁ ችግር" ሁሉ ዩኒቨርሲቲው ሀላፊነት የማይወስድ መሆኑን ይገላፃል" ይላል

ሲጀመር ተማሪ በመገደሉ ምክንያት ስጋት ያደረባቸው ተማሪዎች ከወራቤ ዩኒቨርስቲ ትምህርት አቋርጠው ወደ ክልላቸው መመለስ መብታቸው ነው። መብታቸውን አክብሮ በሰላም ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ደግሞ የዩኒቨርስቲውና የዞኑ ግዴታ ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ ካለ እኔ ፈቃድ ትምህርት አቋርጣችሁ ስትሄዱ ችግር ከገጠማችሁ አያገባኝም ማለት ምን ማለት ነው?!

ከዩኒቨርስቲው ውጭ አደጋ ሊያደርስባቸው ያቀደ የታጠቀና የሸመቀ ኋይል አለ ለማለት ነው?! ወይስ ከወገኑ፣ ከክልሉና ከቤተሰቡ የራቀን ተማሪ ለፖለቲካና ለሐይማኖት ፍጆታ ለማዋል በማሸማቀቅ ለማገት እየተሞከር ነው?! ዩኒቨርስቲውና ዞኑ በአደራ የተቀበሏቸው ተማሪዎች ጉዳይ አያገባኝም ካለ፣ ሌላ ማን የሚያገባው አለ ማለት ነው?! ሌላው ክልልም በተመሳሳይ ሁኔታ የተማሪዎች ደሕንነት እኔን አያገባኝም ቢል ምን ሊከሰት እንደሚችል ዩኒቨርስቲውና ዞኑ አስበብወበት ይሆን ይህ መግለጫው የወጣው?!

ዩኒቨርስቲው ከማንኛውም አደጋና ስጋት ጠብቆ እንዲያስተመርና እንዲያበቃ የተረከባቸው ተማሪዎች መማር አንፈልግም፣ በቃን፣ ስጋት አለብን ሲሉ በክብር ወደ መጡበት መሸኘት እንጂ አደጋ ቢደርስባችሁ አያገባኝም ማለትንስ ምን የሚሉት ቅብጥርጥር ነው?! ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ጊቢ ውጭ ለአደራ ተማራዎች የሚበቃ አስተማመኝ ሰላም ከሌለና ስጋቱ በገደምዳሜ እየተገለጸ፣ ልጆቹን ለአንድም ቀን ቢሆን በዩኒቨርስቲው እንዲቆዩ የሚፈቅድ ቤተሰብ ይኖራል ብሎ መገመትስ አሳፋሪ አይደለም ወይ ?! ዛሬ ልጆቹ በዩኒቨርስቲ መግለጫ ታግተው እያለ ወደፊት ልጆቹን ወደ ወራቤ ዩኒቨርስቲ በአደራ የማልክ ቤተሰብ ይኖራል ብሎ ማሰብስ ንቀት አይሆንም።

እንቀጥል:-

"በወቅቱ በተከሰተው ሁኔታም ይላል የዩኒቨርስታው መግለጫ "የአንድ ተማሪያችን ህይወት ያለፈ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ለተማሪው ቤተሰብ እና ጓደኞች በሙሉ መፅናናትን እየተመኘ ሌሎች ተማሪዎቻችን በዚህ ዓይነት አላስፈላጊ የሆነ ድርጊት ባለመሳተፍ የራሳቸሁን ደህንነት መጠበቅ እንዳላባችሁ በጥብቅ ዩኒቨርስቲው ያስገነዝባል፡፡" ይላልደ

ወራቤ ዩኒቨርስቲ ሟችን በሚመለከት ከገለልተኛ አካል የተጣራ መረጃ ሳያገኝና መንስኤውን ሳይታወቅ፣ ሟች የሞተው አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ በመሳተፉ ማለቱ ማለትስ ምን መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ይሆን። አላስፈላጊ ድርጊት ማለትስ ምን ማለት ነው?! አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ መገኘትስ ሕግ ፊት ያቀርባል እንጂ እንዴት ነፍስን ያሳጣል?! ያውም አዳጊ የአደራ ልጅን ያህል?!

"አላስፈላጊ ድርጊት" በሚል በጅምላ ክስ የተማሪ ሕይወት መጥፋቱ ሳያንስ ወደፊትም ሊጠፋ እንደሚቻል ዩኒቨርስቲው መግለጫ ማውጣቱስ ነውር አይደለም ወይ?! ተማሪዎች ትምሕርት አቋርጠው ከዩኒቨርስቲ ቅጥር ከወጡ ለአደጋ አጋልጧቸው ከማለትስ በምን ይለያል?! ይህንን ዓይነት መግለጫ ማውጣትስ ለአንድ ዞንና ዩኒቨርስቲ ብቻ በተለይ የተሰጠ መብት አድርጎ መውሰድስ ውሎ አድሮ ማጣፊያ አያሳጥርም ወይ ?! ሁሉም ነገር በጠገጉ በቦታውና በልኩ ሲሆን ያኗኑራልና፣ እረ እየተስተዋለ።

አቶ ሙሼ ሰሙ

Ethiomedia

-------------------------
ይህንን ተጭነው ቪድዮውን ይመልከቱ





ይህንን ተጭነው ከቴሌግራም መረጃ ያግኙ https://t.me/ethiomedia2