Get Mystery Box with random crypto!

አቡ ዓብደላህ ግመልህ እንዴት ሆነች? ከወጣት ሶሐቦች ውስጥ አንዱ ነው። ሳይሰልም በፊት ከአን | Ethio iselamic gerup

አቡ ዓብደላህ ግመልህ
እንዴት ሆነች?

ከወጣት ሶሐቦች ውስጥ አንዱ ነው። ሳይሰልም በፊት ከአንዲት ኮረዳ ጋር ለየት ያለ ቅርርብ ነበረው። ኢስላምን ከተቀበለ በኋላ አንድ ቀን በመዲና ጎዳና ላይ ልጂቱ ጋር ተገጣጠሙ። አይኑን ሳይሰብር ፍጥጥ ብሎ፣ አንገቱን ጠምዝዞ እያየ መንገድ ስቶ ከግድግዳ ጋር ተጋጭቶ ደምም ፈሰሰው።

በዚሁ ሁኔታ ረሱላችን ጋር መጣሁ ይላል የዛሬው ኮከባችን ኸዋት ቢን ጁበይር (ረዐ)። ደሜን ሲያዩም "ምን ሆነህ ነው?" ብለው ጠየቁኝ። እኔም ስለሆነው ነገር ሁሉንም ነገርኳቸው ይላል። እርሳቸውም "እንዳይደግምህ። አላህ ለአንድ ባሪያው መልካምን ሲሻለት ቅጣቱን በዱንያ ያፈጥንለታል።" አሉት። (የጅህን ነው ያገኘኸው አሉት ) አይ ! ረሱል

ኸዋታችን አንድ ከበድ ያለ ገጠመኙን እንደሚከተለው ይነግረናል:- ነብያችን (ሰዐወ) ጋር መረ-ዞህራን (ለመካ ቅርብ ስፍራ ነው) የተሰኘ ስፍራ ላይ አረፍን። ካረፍኩበት ድንኳኔ ወጣ ስል ሴቶች ሰብሰብ ብለው ይጫወታሉ። በጣም ተመሰጥኩ። ተመልሼ ዘነጥ የሚያደርገኝን ልብስ ለብሼ ተቀላቀልኳቸው። (ከነርሱ ጋር እየተጫወትኩ፣ ስሳሳቅ) ነብያችን (ስዐወ) ከማረፊያቸው ድንገት ወጡ።

ሲመለከቱኝም "አባ ዓብደላህ ከነርሱ ጋር ምን ትሰራለህ ?" አሉኝ። በድንጋጤ ብርክ ያዘኝ። ምላሴ ተያያዘ። ድብልቅልቅ ያለ መልስ ሰጠኋቸው። ይላል። "አንድ እየደነበረ የሚሮጥ አስቸጋሪ ግመል አለኝ። ለርሱ ማሰሪያ ገመድ ፈልጌ ነው።" አልኳቸው።

እንድነሳ ካደረጉኝ በኋላ ለመፀዳዳት ሲሄዱ ተከተልኳቸው ይላል። ውዱእ አድርገው ከፂማቸው ውሃ እየወረደ መጡና። " አባ ዓብላላህ ግመልህ እንዴት ሆነ?" አሉኝ። ከዚያም ወደ መዲና ጉዟቸውን ቀጠሉ። ነብያችን ከዚያ በኋላ መንገድ ላይ ሲያገኙት ስለ ግመሉ በተደጋጋሚ ይጠይቁታል

መዲና ከደረሱ በኋላ ግን ኸዋት በጣም ስላፈረ ከመስጂድ ቀረ። እርሳቸው (ሰዐወ)፣ መስጂዱና ወንድሞቹ ሲናፍቁት አንድ ቀን ለናፍቆት ጭር ባለበት ሰዓት መስጂድ ገብቶ በተመስጦ ይሰግድ ጀመር። ነብያችንም(ሰዐወ) ከቤት ወደ መስጂድ ገቡና ቀለል ያሉ ረከዓዎችን ሰገዱ። ኸዋት መግባታቸውን ሲያውቅ እስኪወጡለት ድረስ ሰላቱን የባሰ አስረዘመው።

ሐቢባችን (ሰዐወ) ነቄ፣ ምርጥ ሙረቢና አስደናቂ ፍጡር አይደሉ " ኸዋት እንደፈለግክ አስረዝም፣ እኔ እንደሆንኩ ሳትጨርስ ከዚህ አልሄድም" አሉት።
አስቡት ሶላት ውስጥ ምን ሊያስብ እንደሚችል
ራሱ ይነግረናል " በቃ እውነቱን ተናግሬ ልገላገል ብዬ ወሰንኩ" ይላል። ቶሎ አሰላመተና ቀረባቸው። "አሰላሙ ዓለይኩም አባ ዓብደላህ ግመልህ እንዴት ሆነ?" አሉት። እርሱም " በእውነት በላኮት አምላክ እምላለሁ ከዚያ ቀን ጀምሮ ግመሉ አልፈረጠጠም" አላቸው። " አላህ ይዘንልህ" ብለውት ፋይል ዘጉ።

ነብያችን (ሰዐወ) ኸዋት እንዲህ ያለ ግመል እንደሌለው ያውቃሉ። ሴቶች ጋር የተቀመጠውም ቅፅበታዊ በሆነ ሰዋዊ ድክመት ምክንያት እንደሆነ ተረድተውታል። የለህም ዋሽተኸኛልም አላሉትም። ነገርግን በተደጋጋሚዋ ጥያቄያቸው ውስጥ "እውነቱን አውቄያለሁ ተናግራት" እያሉት ነበር። ጉዳዩንም በርሱና በርሳቸው መሃል ብቻ አስቀሩት። ህዝብ ፊት አላሰጡትም።

አማኝም ይሁን አስተባባይ፣ ታዛዥም ይሁን ስህተት ላይ የሚወድቅ ጥፋተኛ፣ አዋቂም ይሁን ጃሂል፣ ሃብታምም ይሁን ድሃ፣ መሪም ይሁን ተመሪ ብንሆን ዞረን ዞረን ሰዎች ነን። በውስጣችን የብዙ ስሜቶች ፍቅር አብሮን ተፈጥሯል። ገንዘብ፣ ተቃራኒ ፆታ ወዘተ። ክደን ሳይሆን በሰዋዊ ስህተት ገብተን እናምፃለን። ወንጀል ከነድንበሩ ወንጀል ነው። በልሳናችን፣ ተግባራችንና ህልውናችን ልንርቅና ልንጠየፈው ግድ ይላል።

እና ምን ለማለት ነው

ያንተ ሚና ሰዎችን ከፈጣሪያቸው ጋር በማስተዋወቅ፣ ጥቅምና ጉዳት በጉልህ ይታዩ ዘንድ የብርሃን ጨረር በመሰለጥ ላይ ብቻ የተገታ ነው። የሰዎችን ነውር ሸፍን እንጂ አታዋርድ። ከቻልክ እዘንላቸው ካልቻልክ ግን አላህ ወደርሱ ተጣሪው እንጂ ፍጡራኑን አላፈናፍን ባይ ተቆጣጣሪ አድርጎ ስላልሾመህ ቦታህንና አቅምህን እወቅ። ኃይማኖተኝነት (አማኝነት) ከሕይወት ራስን ማግለል ሳይሆን በውስጧ ሆኖ አላህ ወደሚፈልገው አቅጣጫ መንጎድ ነው።
አብዱሮህማን ስይድ (ሜጢ)