2022-08-29 10:00:17
ሽ ል ን ጌ ን
══❁══
ተስፋዬ ገሰሰ
'
ባቡሩ መንቀሳቀስ ሲጀምር
«ኧረ ሽልንጌን ... ሽልንጌን» እያለች ትጮኽ ጀመር። ከባቡሩ ሞተር ግምግምታና ከተሳፋሪዎቹና ከሻጮቹ ጫጫታ በላይ ለማሰማት የሚጣጣር ኡኡታ ነበር።
«ሽልንጌን ... ኧረ ሽልንጌን!» ባቡሩ ኃይለኛ ፊሽካውን በሞተሩ 'ጃስ ጃስ' ላይ አከለበት። የተንጠላጠሉት ሻጮች ጡብ ጡብ እያሉ ወረዱ። ፍጥነቱ ሲጨምር፣ ግስገሳው ሲቀጥል በዚያው መጠን የአሚና አቤቱታ እየቀነሰ፣ ወደኋላ እየቀረ ሄደ።
ፓፓያ የያዘችበትን እንቅብ ከራሷ ላይ እንዳስቀመጠችው እየሮጠች ብትጮህም አልደረሰችበትም። ባቡሩ ፊኛውን እያስተነፈሰ መጎተቱን ቀጠለ። የኑሮዋን መኖ የያዘው የብረት ዘንዶ እየተምዘገዘገ ሲፈተለክ እጆቿን ወደ ሰማይ እያርገበገበች ተንበርክካ እንባ በተቀላቀለበት ድምፅ «ሽልንጌን ... ወይ ሽልንጌን» ሳታውቀው በሀዘኑ ጭነት ራሷን ስትደፋ የፍሬው እንቅብ ተንሸራቶ ከፊቷ ወደቀ። ፓፓያዎቹም እንደ እምቧይ እየተንከባለሉ በሀዲዱ ላይ ወደቁ።
አሚና ጠና ያለች የአርባ አምስት ዓመት ሴት ነበረች። የረር ጣቢያ አጠገብ ተወልዳ ለአቅመ ሄዋን እስክትደርስ ድረስ፣ ከቤተሰቦቿ ጋር ከብት እያገደች ስትኖር ከተዳረች ወዲህ፣ ባለቤቷ ከተማ ሄዶ የቀን ሥራ እየሠራ መኖርን ስለመረጠ ያላቸውን ከብቶች ሸጠው የረር በጭሰኝነት አንዲት ዳስ ሠርተው ተቀመጡ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለጥቂት ጊዜ ታሰቃየው የነበረችው ወባ ባለቤቷን ነጥቃ ወሰደችው።
በባህላቸው መሰረት የባሏ ወንድም መጥቶ 'አግብቼ ልውሰድሽ' ቢላት፣ ከዘላንነቱ የከተማውን ሕይወት መርጣ ብቻዋን ቀረች። ከዚያም በኋላ ታናሽ እህቷ ፋጡማ ከባሏ ሸሽታ መጥታ ጥቂት ጊዜ አብረው ከኖሩ በኋላ "እዚህ መጥቶ ካገኘኝ ይገለኛል" ብላ ጥላት በባቡር ወደ ድሬዳዋ ወረደች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሚና ብቻዋን ትኖራለች። ዳሌዋ ሳይሟሽሽ፣ የደረቷ ፍሬ ሳይጠወልግ በፊት አብሮ አዳሪ ነበራት። በመጠኑም ጥቅም ታገኝ ነበር። ግን በመጨረሻ ካንዱ ከባቡር ዘበኛ ወንድ ልጅ ካገኘች በኋላ ዕድሜም ተጫናት፣ ፈላጊዋም ጠፋ። እሷና ልጇ አብርሽ ብቻቸውን ቀሩ። አብርሽ አምስት ዓመት ሲሆነው አክስቱ ፋጡማ መጥታ አባብላ ድሬዳዋ ወሰደችው።
ፋጡማ በድሬዳዋ የጥጥ ፋብሪካ ሠራተኛ ናት። በወር የምታገኘው ገቢ ሠላሳ ብር ብቻ ነበር። ከዚያ ውስጥ በየሳምንቱ አንድ አንድ ብር እቁብ ትጥላለች። በዚህ ሁኔታ ከሠላሳ ብር ደመወዝ ውስጥ አስቀርታ ባጠራቅመችው ገንዘብ ጨርቃ ጨርቅና ምግብ ለአሚና እና ለልጇ ይዛ መጣች።
ፋጡማ ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ልጅ እንዲኖራት ትፈልግ ነበር። ግን እንደ እህቷ አልታደለችም። ስለዚህ አሚና ከነልጇ ወደ ድሬዳዋ ይዛት ሄዳ ሥራ ፈልጋላት አብረው እንዲኖሩ ብትለምናት፣ ለአሚና የረርን ለቅቆ መሄድ አልታይሽ አላት። በመጨረሻም «አንቺ እንኳን ባትሄጂ ልጅሽን ወስጄ ላስተምረው እኔ እንደምታዪኝ ልጅ የለኝም» ብላ ብትለምናት «እሱ እሺ ካለሽ ውሰጂው» አለቻት።
አሚና ምንም ቢሆን እኔን እናቱን ጥሎ አይሄድም። አልፈልግም ብሎ ይቀራል ብላ ተማምና ነበር የተናገረችው። ፋጡማ ግን አብርሽን ለሆዱ ባቀረበችለት ምግብና ለገላው ባለበሰችው ቆንጆ ልብስ እንዲሁም በዓይነ ህሊናው በሳለችለት የድሬዳዋ ከተማ ብልጭልጭነት አባብላ 'ከፋጤ ጋር እሄዳለሁ' ብሎ እናቱን ውጥር አድርጎ እንዲይዛት አስገድደችው። አሚና እምቢ ብትል እንኳን የልጁ ለቅሶ አፋጦ ያዛት። «ፋጤ ... ወጂን ዴምና።» እያለ አላስገባ፣ አላስወጣ አላት። መለየቱ የእናት አንጀቷን የሚቆርጠው ቢሆንም፤ ከሷ ጋር ተቆራምዶ ከሚኖር አክስቱ ጋ ድሬዳዋ ቢወርድ ቀን ይወጣለት ይሆናል ብላ በማመን ጨክና ወሰነች።
አንድ ቀን አቅፋው ካደረች በኋላ ማለዳ ጠዋት የአዲስ አበባ የሌሊት ባቡር ሲገሰግስ ደረሰ። ሦስት ቀን ብቻ እንድታርፍ የተፈቀደላት ፋጡማ ለእረፍቷ ማለቅ አንድ ቀን ሲቀራት ማታውኑ እቃዋን አደራጅታ፣ ገና ባቡር ሳይደርስ ነቅታ፣ ልብሶቿን ለብሳ፣ አሚናንም ቀስቅሳ ትጠባበቅ ነበር። የባቡሩ ድምፅ ገና ከሩቅ ከሀዲዱ እያስተጋባ ሲሰማ፣ አብርሽን ከእናቱ እጅ ላይ መንጭቃ ወሰደችው።
አብርሽ እንቅልፉን አልጠገበም ነበር። እናቱም ወደ ፉርጎው ውስጥ ሲገባ በፋጡማ እጆች ውስጥ እንዳለ ሲያዛጋና ዓይኖቹን ሲያሻሽ ተንጠልጥላ አቀፈችውና ሳመችው። "ልቀቂው ባቡሩ ተነሳ" ብላ መንጭቃው ወደ ውስጥ ገባች። በእናቱ ዓይን እንባ ሞላ። የባቡሩ ፊሽካ ከሩቅ የሚጮህ መሰላት። ከፊት ለፊቷ የብረት ቤት እየተምዘገዘገ አንዱ አንዱን እየተከተለ ሲያልፍ ህልም እንጂ እውን አልመሰላትም። ወዲያው ከፊቷ ባዶ ሲሆን ባነነች።
>>>
#ሽልንጌን
@ethiobooks
814 viewsተስፋዬ መብራቱ, 07:00