Get Mystery Box with random crypto!

እንጀራ እንደ - - - '- - - ምን?' እንዳትሉኝ፤ እንጀራ - ማለቴ የሻገተ እን | ከስነ-ፅሁፍ ዓለም

እንጀራ እንደ - - -


"- - - ምን?" እንዳትሉኝ፤ እንጀራ - ማለቴ የሻገተ እንጀራ የበሽታ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል እናንተም ትገምቱ ይሆናል። ሁላችንም እንጀራ በሊታዎች ነን ካልን በተለያየ ጊዜ የሻገተ እንጀራ የመጠቀም ዕድላችን በማወቅም ባለማወቅም ያጋጥማል። ያው እንደምትውቁት በአብዛኛው የሻገተ እንጀራ ሻገተ ተብሎ አይጣልም። ወይ በፀሐይ፣ ወይ በሙቀት ደርቆ የድርቆሽ ፍርፍር ሆኖ ይቀርባል።

አንዳንዶቻችን ቤት ደሞ "ለልጅ ምንም አይለው" ተብሎ ይሰጠናል። አሊያም "የእንጀራ ጡር አለው" ተብሎ ወይ ለኔ ብጤ አሊያም ለቤት እንስሳት በመኖነት ይቀርባል። ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው። የሻገተ እንጀራ የሚያስወግድ አንጀት ስለሌለን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንጠቃለን።

ሻጋታ የፈንገስ ዓይነት ነው። ፈንገሱም በውስጡ 'Aflatoxin' የሚባል አደገኛ መርዛማነት ያለው ንጥረ ነገር ይዟል። ይህ 'አፍላቶክሲን' የሚያስከትለው ጉዳት እንደ ግለሰቡ እድሜ፣ ፆታ፣ የመርዙ መጠን፣ የተጠቃበት ጊዜ (Duration)፣ የግለሰቡ የጤና ደረጃ፣ የሚኖርበት አካባቢ ሊለያይ ቢችልም ጎጂነቱ ግን ምንም የማያወላውል ነው።

ባጠቃላይ በዚህ ከሻጋታ የሚገኘው መርዝ ሰዎችን በሁለት መንገድ ይጎዳል።
አንደኛው፦ ከፍተኛ መጠን ያለውን መርዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወሰድን ከሆነ ለጉበት በሽታ፣ ለካንሰር፣ ለአእምሮ ዘገምተኝነት፣ ለሆድ ህመም፣ ለሳንባ እና ለአጠቃላይ የሰውነት እብጠት እንዲሁም ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
ሁለተኛው፦ ደግሞ አነስተኛ መጠን ያለውን መርዝ ለረዥም ጊዜ መውሰድ ሲሆን ይህም በተለይ ከእንጀራ ጋር በተያያዘ፣ በኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ሊከሰት የሚችለው ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአካላዊ እድገት ዘገምተኛነትና የጉበት ካንሰር ሊያስከትል እንደሚችል በሰፊው ይታመናል። ምናልባት የኛ ሀገር ልጆች ኮሳሳ መሆንና የጉበት ካንሰር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣት፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለኝ።

በዚህ በኩል ጥናቶች ቢሠሩ እውነቱ ፍንትው ብሎ ሊወጣ እንደሚችል እያመንኩ፤ እንጀራን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የሻገቱ የምግብ ዓይነቶችን በሰውም ሆነ በእንስሳት መኖነት መጠቀም ጠንቁ ብዙ መሆኑን ተገንዝበን፤ በተለይ ሕፃናትን ከነዚህ ዓይነት ምግቦች መከላከል ችላ የማይባል ጉዳይ እንዲሆን አሰምርበታለሁ!!
>>>
ገፅ 75 - 76
━━━━━━━━━
ጤና፣ ነገር እና ጉዳይ
ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ

https://t.me/Ethiobooks