Get Mystery Box with random crypto!

ጥላሁን ገሠሠ እኔ እንደማውቀው     ════•✦•════ መስፍን ሀብተማርያም ' >>> | ከስነ-ፅሁፍ ዓለም

ጥላሁን ገሠሠ እኔ እንደማውቀው
    ════•✦•════
መስፍን ሀብተማርያም
'
>>>
ጥላሁን በጣም ውድ መኪኖችን ባልያዘበት ጊዜ በ70ዎቹ መጀመሪያ እየተበላሸች ታበሳጨው በነበረችው ሬኖ መኪናው እኔንና ብዙ ግጥሞች የገጠመለትን ክፍለ ኢየሱስ አበበን ይዞ ከወደ ለገሀር ስንመጣ ቸርችል ጎዳና ላይ መብራት አቆመን። መኪና ሲነዳ "ጎራው"ን፣ "ጉብልዬ"ን፣ "መላመላ"ን ለራሱ ማንጎራጎር ይወድ ነበር።

ከእነዚህ አንዱን ይመስለኛል ሲያንጎራጉር አረንጓዴ ሜርሰዲስ መሪ የጨበጠች አንዲት ቆንጆ ልጅ ፍዝዝ ብላ ስታዳምጥ አየን። ወዲያው ቀዩ ጠፍቶ አረንጓዴው በራ። መኪኖቹ ጉዞ ሲቀጥሉ ወጣቷ «ጥላሁን እንጉርጉሮህን ቀጥል፣ አትንቀሳቀስ። የትራፊክ እኔ እቀጣለሁ» ስትል ተነስተን ሄድን። ጓደኛዬ «ህ! ያንተ ድምጽ መኪናም ውስጥ ይፈለጋል፣ ቀይ መብራት ላይ እንኳ። አይ መታደል!» አለ። ...
-
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን መረዳጃ ማኅበር በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አነሳሽ መሆንም ደስታው ነው። አንድ ጊዜ አሥር የምንሆን ሰዎች የመረዳጃ ማኅበር መሥርተን በነበረበት ወቅት እኔ የማኅበሩ ፀሐፊ ሆኜ ሕጉን ባረቅም በጠቅላላው ማኅበሩ ይንቀሳቀስ የነበረው በጥላሁን የቃል ሕግ ነበር።

እሱ ያለው ይፀድቃል! እሱ ያወገዘው ይሰረዛል። የሚያቀርባቸው ሃሳቦች የምናምንባቸው ቢሆኑም በአብዛኛው የሚገዛን ድምፁ ነበር። ከተጨቃጨቅን ሲያንጎራጉርልን ዝም እንላለን። ስብሰባ አቋርጦ መሄድ የሚፈልግም ካለ እሱ ሲያንጎራጉር ቁጭ ይላል።

ሦስት ዓመት ከቆየንበት የማኅበሩ ግንኙነታችን ገንዘብ ለማሰባሰብ የጥላሁን ዜማ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በኋላ «አንድ ዘፈን ስትጠይቁ ለማኅበሩ ሁለት ብር አስቀምጡ፣ ድጋሚ ስትጠየቁ አንድ ብር ያስጨምራል» የሚል ደንብ አወጣና የብር ዓይነት ጠረጴዛው ላይ ይከመር ጀመር። የደሞዝ ሰሞን ቢያንስ ብር 30 የማያወጣ አልነበረም። በአንድ ቀን ብር 70 ያስቀመጠም ከመካከላችን ነበር።

ጥላሁን ብዙ ብር እንድናዋጣ ሆን ብሎ ዘፈኑን ያሳጥረዋል። ያኔ ድጋሚ እንጠይቃለን። ካፒታላችን ትንሽ ቢሆንም የመረዳዳት ጅምራችን የሚያበረታታ ነበር። በኋላ ግን በቀይ ሽብር ምክንያት መሰባሰብ አደገኛ እየሆነ ስለመጣ ለጊዜው ተበታተንና የማኅበራችን ነገር አከተመለት።
-
በመጨረሻም የጥላሁን ዜማ በአንድ ምሽት ያመጣውን ውጤት ልገልፅላችሁ እወዳለሁ። ካዛንቺስ ያለ ጓደኛችን ቤት ሆነን ስናወጋ በድንገት አንድ ሴት ከጎረቤት ሮጣ መጥታ ሳሎኑን አቋርጣ መኝታ ቤት ስትገባና በሩን ስትዘጋ ባልዬው ተከትሎ መጣ። ጥላሁን «የጠላሽ ይጠላ» የሚለውን ዘፈን ያንጎራጉር ነበር። በስሜት ተውጠን እርጭ ብለን እያዳመጥነው ያንቆረቁረዋል። ባልዬው ልክ ተንደርድሮ ሲገባና ገላጋዮች ሲይዙት ሰውዬውን እያየ ጥላሁን ገና በካሴት ያላስቀረፀውን ዜማ ጣራው እስኪሰነጠቅ ይለቀዋል።

ሰውዬውም «ጥላሁን አለ እንዴ?» አለና እንደ መደንገጥ ብሎ ፊቱን ወደ እኛ አዞረ። አርቲስቱ ግን ቀጠለ። ሰውዬው ቁጭ አለ። ጥላሁን በዚህ ጊዜ (ሰውዬው ቁጭ ሲል) ዘፈኑን አቋረጠ። በሚያሳዝን አስተያየት መሬት መሬት እያየ «ወይ ቅዱስ ገብርኤል የጥልዬን ድምፅ ልስማበት ወይስ የእሷን ለከፋ» አለ። አንድ ጊዜ ሳቃችንን ለቀቅነው።
>>>
━━━━━━━━
የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም

https://t.me/Ethiobooks