Get Mystery Box with random crypto!

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሄ | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሄደ ።

ህዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የክፍለ ከተማ ንግድ ፅ/ቤት ሃላፊዎች፣ የመንግሥት ፕሮጀክት አስገንቢ ተቋማት እንዲሁም ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎችና አከፋፋዮች በተገኙበት በሲሚንቶ ግብይት፣ ስርጭትና ቁጥጥር ላይ ውይይት አካሂዷል ።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ አሁን እየታየ ያለውን የሲሚንቶ ምርት እጥረትና ሰው ሠራሽ የሆነ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በዋናነት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት መሆኑን ገልፀው የፋብሪካዎችን ምርት ማሳደግና ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ ክትትል በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል ።

አቶ አደም ኑሪ የከተማው ንግድ ቢሮ ሃላፊ በበኩላቸው ለተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረትና ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ምክንያት በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልጉ አካላት የፈጠሩት መሆኑን ገልፀው፤ ለከተማው የተመደበውን ኮታ አጠቃቀም ለማሳደግና የቀረበውን ምርት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል ያሉትን አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ የማንሳት አቅምን ከፍ ለማድረግ የመንግስት ፕሮጀክት የሚያስገነቡ ተቋማት፣ ሲሚንቶን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አምራቾችና ስትራቴጂክ ፋይዳ ያላችው የግሉ ሴክተር በቀጥታ ከፋብሪካ እንዲያነሱ፤ በሌላ በኩል አነስተኛ ፍጆታ ያላቸው ተጠቃሚዎች ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ልማት ድርጅትና ከኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን እንዲያነሱ በተጨማሪም በቅድመ ክፍያ ያልተነሳ ምርት ያላቸውን አከፋፋዮች የሚያነሱት በተተመነ ዋጋ በቸርቻሪዎች በኩል ለህዝብ እንዲደርስ የስርጭት መስመር የተዘረጋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በዚህ መልኩ በከፍተኛ ጥረት ወደ ከተማው የሚገባው ምርት ለታለመለት ፕሮጀክት ብቻ እንዲውል ፋብሪካዎች፣ አስገንቢ ተቋማት፣ አከፋፋይ ድርጅቶችና የንግድ ቢሮ በቅንጅት ክትትል ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ አላስፈላጊ ተጠቃሚነትን ለመከላከል የምርት ስርጭቱ ኦዲት እንደሚደረግና ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የክትትል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ውዝፍ ምርት የሚያነሱ አከፋፋዮች ቢሮው ያዘጋጀውን የስርጭት ውል ተዋውለው ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪ አስተላልፈው ከዚህ ውጪ ለሚንቀሳቀሱት በሚኒስቴሩ እና በፋብሪካዎች በኩል ተገቢው እርምት እንዲወሰድ ጠይቀው ይህ ሳይሆን ቀርቶ ምርት ሲያዝዋውር የተገኘ አካል መስከረም 05/2015 በወጣው የህዝብ ማስታወቂያ መሰረት እንደሚወረስ አክለው ገልፀዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወካይን ጨምሮ በመድረኩ የተሳተፉ አካላት ለስርጭት እጥረትና ለዋጋ ንረቱ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ