Get Mystery Box with random crypto!

ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት የውስጥ አሠራር ሥርዓት ባላከበሩና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ ሠ | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት የውስጥ አሠራር ሥርዓት ባላከበሩና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ወሰደ

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2014 በጀት ዓመት አሠራርን፣ አገልግሎት አሰጣጥን፣ ሀብት አጠቃቀምንና መልካም አስተዳደርን በተመለከተ ከውስጥና ከውጭ ደንበኞች የቀረቡ 469 ጥቆማዎችን በመቀበል በ247 (73%) አመራርና ሠራተኞች ላይ የማጣራት ሥራዎች በማካሄድ በ54ዎቹ ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርጓል። በሌሎች 12 የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ላይ ደግሞ በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አማካኝነት ጉዳያቸው በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

እምነት በማጉደል ስርቆት መፈጸም፣ የሥራ ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡና በታማኝት አለመወጣት፣ ቅጥር፣ ዝውውርና ደረጃ ዕድገት ማጓተት፣ የሰዓት መቆጣጠሪያ ላይ አስቀድሞ መፈረም፣ የጥገና አገልግሎት መጓተት፣ ያለ ፍቃድ ከሥራ መቅረት፣ የደንብ ልብስ የጥራትና የሥርጭት አሠራር ክፍተት መኖር፣ ከመመሪያ ውጭ የተለያዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች መፈጸም፣ በሥራ ገበታ አርፍዶ መገኘት፣ ተገቢ ያልሆነ የጥቅማጥቅም ክፍያ መፈጸም፣ በሀሰት የትምህርት ማስረጃ መገልገልና ያለበቂ ምክንያት ሥራን ማዘግየት የሚሉት ከውስጥና ከውጭ ተገልጋዮች የቀረቡ ጥቆማዎች ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸምና ሚዛን ማጉደል፣ ሥራ በማጓተት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም መጠየቅ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የተቃረቡ ምርቶች ግዥ መፈጸም፣ በሥራ ሰዓት የመሸጫ ሱቆች ከፍቶ አገልግሎት ያለመስጠት፣ ሥራን በአግባቡ ባለመወጣት ምርት ማጉደል፣ የገቢ ሂሳብ ሪፖርት በጥራትና በጊዜ ገቢ አለማድረግ፤ የክፍያ ሰነድ ትክክለኝነት ሳይረጋገጥ ለክፍያ መምራት፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ በወቅቱ ገቢ አለማድረግ፣ በአገልግሎት ስታንዳርድ መሠረት አለመምራትና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ላይ ክፍተት መኖር በኮርፖሬሽንና በሌሎች አካላት የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ባለማድረግ የተፈጸሙ የአሠራር ክፍተቶች ሆነው የቀረቡ ጥቆማዎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከደንበኞች የመጣውን ጥቆማ ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሠራር ሥርዓት ያላከበሩና የሥነ-ምግባር ጥሰት የፈፀሙ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ፣ የገንዘብ ቅጣት፣ ከኃላፊነት ቦታ ከማንሳት እስከ የሥራ ስንብት የሚደርሱ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህም 8 የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 12 የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 17 የደመወዝ/ገንዘብ ቅጣትና የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም 12 የሥራ ስንብት እርምጃ መወሰዱን ከኮርፖሬት ሥነምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡