Get Mystery Box with random crypto!

መስከረም 24፣ 2015 ከሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ውጪ ሲዘዋወር ነበር የተባለ ከ22,000 ኩንታል | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

መስከረም 24፣ 2015

ከሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ውጪ ሲዘዋወር ነበር የተባለ ከ22,000 ኩንታል በላይ ሲሚንቶ ተይዞ እርምጃ መወሰዱ ተነገረ፡፡

ይህንን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ነው፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋ እጥረትን ለመቆጣጠር የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ለከተማው የተመደበው ሲሚንቶ ከተቀመጠው አሰራር ውጪ ገበያ ላይ እንዳይውል ከኦሮሚያ ልዩ ዞን እና ከኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ጋር በትብብር ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የከተማው የንግድ ቢሮ ሀላፊ አቶ አደም ኑሪ እንደተናገሩት በተሰራው የቁጥጥር ስራ 22,293 ኩንታል ሲሚንቶ ከመመሪያው ውጪ ሲዘዋወር ተይዟል፡፡

ቢሮው በመግቢያ በሮች ከሚያደርገው ቁጥጥር በተጨማሪ በከተማው ውስጥ በሚገኙ የንግድ ቤቶች፣ የተጀመሩ የግንባታ ስራዎች እንዲሁም የሲሚንቶ ማከማቻ ስፍራዎቹ ባደረገው ፍተሻ መያዙ ተነግሯል፡፡

ከተያዘው ውስጥ 15,179 ኩንታል ተወርሶ በኢ.ግ.ል.ድ እና በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ለገበያ ቀርቦ መሸጡን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡

2,266 ኩንታሉ ደግሞ ተጣርቶ ህጋዊነቱን የሚያረጋግጥ መረጃ በመቅረቡ ተለቋል ቀሪው መንግስት በተመነው ዋጋ እንዲሸጥ ሆኗል ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ ምርትን በቀጥታ ከፋብሪካዎች ገዝተው እንዲጠቀሙ በመመሪያው የተፈቀደላቸው ተቋማት የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የውሃ ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የሜጋ ግንባታ ፕሮጀክት ጽ.ቤት የመንገድና ባለስልጣን እና የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ናቸው ተብሏል፡፡

ከዚህ ውጪ በአዲስ አበባ ላለው የሲሚንቶ ፍላጎት ከፋብሪካዎች በመረከብ በችርቻሮና በጅምላ የሚያቀረቡት የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) እና የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ብቻ ናቸው ብሏል ቢሮው በመግለጫው፡፡

ቴዎድሮስ ወርቁ

(ሸገር ኤፍኤም 102.1 ራዲዮ)