Get Mystery Box with random crypto!

ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል የፈጸመ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ በእስርና በገንዘብ ተቀጣ አቶ | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል የፈጸመ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ በእስርና በገንዘብ ተቀጣ

አቶ ሙሉጌታ ጃሌ የተባለ በደሴ ቅርንጫፍ የሸዋሮቢት ግብይትና ክምችት ጣቢያ ሠራተኛ ሆኖ ሲሰራ በህዝብና በመንግስት የተሰጠው አደራ ወደ ጎን በመተው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የመንግስት ንብረት በማጉደል በፈጸመው የሙስና ወንጀል የእስርና የገንዘብ ቅጣት ተወሰነበት፡፡
የኮርፖሬት የውስጥ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ባደረገው ጥልቅ የሰነድ ምርመራ ግለሰቡ ከተረከበው የመንግስት የእህል ምርት ውስጥ ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምርት በህገ ወጥ መንገድ ከመጋዘን አውጥቶ በመሸጥ ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መፈጸሙ በማስረጃ ይረጋግጣል፡፡ ይህን የኦዲት ግኝት መሠረት በማድረግ የኮርፖሬት የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በ|ላ ክስ ለመመስረት የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ጭብጦችን በማዘጋጀት ወንጀሉ እንዲመረመርና ክስ እንዲመሰረት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን ለሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊሰ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ጥያቄ ያቀርባል፡፡
የምርመራ ጥያቄው የቀረበለት የሰሜን ሸዋ ፖሊስ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ክፍል በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት አቶ ሙሉጌታ ጃሌ የፈጸሙት የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀልን በጥልቀት በመመርመር ተጠርጣሪውን ተከታትሎ በመያዝ ለህግ ያቀርባል፡፡
የክስ መዝገቡም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ የደብረብርሃን ምድብ ማስተባበሪያ ተልኮ አቃቤ ህግም ክስ አቀርቦ ሲከራከር ቆይቶ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዕለቱ በዋለው ችሎት በጉዳዩ ላይ ግራና ቀኙን ካከራከረ በኃላ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ማስተባበል ባለመቻሉና በከሳሽ በኩል የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ግለሰቡ ከፍተኛ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል መፈጸሙ ስለታመነ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል ብሎ ባመነበት ተከሳሽ ከኮርፖሬሽኑ እምነት በማጉደል የዘረፈውን ብር 2.890,031 (ሁለት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና ሺህ ሰላሳ አንድ ብር) ከወጪና ኪሳራ ተሰልቶ እንዲከፍል፣በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትና በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ከዚህ ግለሰብ ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ድርጊት፣የክስ ሂደትና የፍርድ ውሳኔ መገንዘብ የሚቻለው ማንኛውም ግለሰብ የማጭበርበር የሙስና ወንጀል በመፈጸም የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን ወስዶ ለጊዜው ከህግ ተሰውሮ ቢቆይም ወቅቱን ጠብቆ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል የጥንቃቄ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ስለዚህ በሚከተሉት የጥቆማ መስጫ መንገዶች ጥቆማ፣ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማቅረብ የምትችሉ መሆኑን በቅድሚያ እናሳውቃለን፡፡
በመደበኛ ስልክ፡-011 416 88 94 በተንቀሳቃሽ ስልክ፡-09 11 96 65 09, 09 11 65 96 96 - ፖ.ሳ.ቁ፡-3321
የኮርፖሬት ሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት