Get Mystery Box with random crypto!

የኔ الله የኔ አላህ ሰሚዕ ነው፤ ያልተናገርነውን፤ ለመናገር ያሰብነውን የሚሰማ፤ ሰፍፍፍ | ᎷUᏚᎯᏰ™ Islamic Page

የኔ الله

የኔ አላህ ሰሚዕ ነው፤ ያልተናገርነውን፤ ለመናገር ያሰብነውን የሚሰማ፤ ሰፍፍፍ ብሎ የሚያዳምጠን፤ ባሪያዬ ምን ጠየቀኝ ብሎ የሚጓጓ፤ እህ የሚለን! እገሌ ጉዳዩን አውጉቶኝ ነበር እጥፍ ድርብ አድርጌ ላንበሽብሸው የሚለን! አይ የኔ አላህ! የሱ ባህሪ እኮ የሚገርም ነው።

አንዳንዴ እራሴን እወቅሳለሁ፤ ሀዘን ሲገባኝ ተቀዳሚ ስሞታዬን የማቀርበው ለጌታዬ ሳይሆን ይቀራል፤ ቅርብ ጓደኞቼን አስቀድማለሁ፤ ቀድሞ መስማት ያለበትን ረስቼ ለቀጣዬቹ አሰሙታለሁ።

ጌታዬ ሰልቺ አይደለም፤ ቀኑን ሙሉ ብናለቅስበት ሳይሰለች ይሰማናል። ሁሉንም ነገር እንጠይቀው ይሰጠናል። 'እቺን ትንሽ ነገርማ አላህን መጠየቅ አፍራለሁ' አትበል! እሱ በየትኛውም ጉዳይ እንድታወጋው በጉጉት እየጠበቀህ ነውና! ለእሱ ምንም ብትነግረው አያሳፍርህምና!

አላህዬ ሀዲሰል ቁድሲይ ላይ ልብ በሚሰረስር ሁኔታ እንዲህ ይላል:
"የአደም ልጅ ሆይ! ከምንም ነገር ፈጠርኩህና አስገኘሁህ፤ መስሚያ፣ ማያ፣ልቦናና ህሊና ሰጠሁህ። እኔ አስታውስሃለሁ አንተ ትረሳኛለህ። እኔ ካንተ አፍራለሁ አንተ ከኔ አታፍርም። በሬን አንኳኩቶ ያልከፈትኩለት ማን አለ? ለምኖኝ ያልሰጠሁትስ ማን አለ? ስስታም ሆኜ ነው እንዴ ባሪያዬ በኔ የሚሰስተው?" ይለናል

ቃላቶቹ አይከብዱም? ሚዛናቸው ከባድ ነው፤ ላስተነተናቸው ጠጣር ምንነት አላቸው፤ ለተረዳቸው ወደ አላህ ለመሮጥ ሰከንዶችን የማይጠይቁ ናቸው!

አያችሁ አስ-ሰሚዕ የኛን ስሞታ ለመስማትና ለመቀበል ምን ያክል ጉጉ እንደሆነ? ባሪያው እጁን ዘርግቶ ሲለምነው በባዶ መመለስን የሚያፍር አምላክ! ሱብሃነላህ ልዕልናህ!

وَاللَّهُ يَسْمَعُ تَحَاوُرَكُمَا ۚ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ بَصِيرٌ

አላህም (በንግግር) መመላለሳችሁን ይሰማል፡፡ አላህ ሰሚ ተመልካች ነውና፡፡"