Get Mystery Box with random crypto!

ሀይለኝነት ====== ፍሮይድ ሁሉንም የሰው ልጅ ፀባይ የሚነዳው ፅታዊ ፍቅር (Eros) ነው ብሎ | Mental wellness የአእምሮ ጤና

ሀይለኝነት
======
ፍሮይድ ሁሉንም የሰው ልጅ ፀባይ የሚነዳው ፅታዊ ፍቅር (Eros) ነው ብሎ ብዙ ሳይቆይ አንደኛው የአለም ጦርነት ይቀሰቀሳል፡፡ በጦርነቱ ላይ የተመለከታቸው ዘግናኝ ትዕይንቶች የሰዎችን ፀባይ የሚወስን ከፆታዊ ፍቅር ሌላ ሀይል እንዲገነዘብ አድርጎታል-ሀይለኝነት (Thanatos)፡፡ ሀይለኝነት ከሰው ውጭ ሌሎች እንሳሳትም ላይ ይስተዋላል፡፡ ሀይለኝነት በተገቢው ቦታና ሁኔታ ሲሆን በህይወት ለመቆየት አስፈላጊ ሲሆን ያለ ቦታው ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት አለው፡፡

ዘመናዊነት የሀይለኝነትን ስሜት ቢያዳፍነውም ለማዳ ቢያደርገው እንጂ አያጠፋውም፡፡ የሀይለኝነት ምክኒያት ስነ ህይወታዊ ወይም ስነ ልቦናዊና ማህበረሰባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ የሀይለኝነትን ስነ ህይወታዊ(ተፈጥሯዊ) ምክኒያቶች ለመረዳት ሁለት ልጆች ያሏትን እናት በልጆቿ መካከል ገና በህፃንነት ያለውን ልዩነት መጠየቅ በቂ ነው፡፡

ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ምክኒያቶቹ እንደሚከተለው ይከፋፈላሉ፡፡

1. መገልገያ፦ ሀይለኝነትን የሚያሳዩበት ዋና አላማ ክፋት ሳይሆን የሚፈልጉትን ለማግኘት ነው፡፡ ስጋ እየበላ ያለ ውሻ ሀይለኝነት የሚያሳየው ምግቡን ለመከላከል ነው፡፡ የማጅራት መቺ ሀይለኝነት አላማው ሌብነት ነው፡፡

2. ፍርሀት፦ አደጋ ሊደረርስ ከመሰላቸው እንስሳት ሀይለኛ ይሆናሉ፡፡ በሰዎችም በተመሳሳይ 'ማጥቃት መከላከል ነው !' በሚል በፍርሀት ምክኒያት ሀይለኝነት ሊኖር ይችላል፡፡

3. ድንበራዊ፦ ይህ አንዳንድ ጊቢዎች ውስጥ ከሚገኙት 'ሀይለኛ ውሻዎች' እስከ የታሪክ መፅሀፍትን የሞሉትን ጦርነቶች ላይ የሚታየውን ሀይለኝነት ያስረዳል፡፡ ድንበር!

4. ወንድነት፦ በአብዛኛው እንሳሳት ወንዶች ላይ የሚታይ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ሀይለኝነት ነው፡፡ በሰው ላይ የሚታዩት ምሳሌዎች የአደባባይ ሚስጥር ስለሆኑ አልፌዋለሁ፡፡

ሀይለኝነት ላይ አካባቢያዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ልጆችን ሀይለኝነት ከሚያሳዩ ፊልሞችና ጌሞች መጠበቅ የወላጆች ሀላፊነት ሲሆን ከፍ ያለ ሀይለኝኘት ለሚያሳዩ ልጆች በማህበረሰቡ ተቀባይነት ባለው መልኩ በተለይ በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዲያውሉት ማገዝ ጥሩ ነው፡፡

ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው