Get Mystery Box with random crypto!

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ግፊት (Hypertension in pregnancy) ይህ የእርግዝና ጊ | Doctor M nursing Home care

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ግፊት (Hypertension in pregnancy)

ይህ የእርግዝና ጊዜ ግፊት 10% የሚሆነው እርግዝና ላይ የሚከሰት ሲሆን

እርጉዝ እናት ላይ ከፍተኛ ችግር ከሚፈጥሩት እና ለሞት በመዳረግ ከሚታወቁት ከማህፀንና እንግዴ ልጅ ደም መፍሰስ እና ኢንፌክሽን ቀጥሎ በሶስተኛነት የእናት ሞትን በማምጣት ይታወቃል።

አንዲት እርጉዝ እናት መቼ ነው ግፊት አለባት የሚባለው?

አንዲት እርጉዝ እናት ግፊት አለብሽ የምንለው ግፊቷ ከ 140 በ 90 በላይ ሲሆን ይህም ማለት የላይኛው ግፊት(systolic) ከ 140 እና ከዛ በላይ የታችኛው(Diastolic) ከ 90 እና ከዛ በላይ ከሆነ ፤ ይህም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሁለት ጊዜ ልኬት በ4 ሳዓታት ልዩነት መሆን አለበት።

የእርግዝና ጊዜ ግፊት ለመባል ግፊቱ የተከሰተው ከ 20 ሳምንት(ከ 5 ወር) በውሀላ መሆን ይኖርበታል።

አንዲት እርጉዝ ሴትን በእርግዝና ጊዜ ለግፊት የሚያጋልጧት ነገሮች ምንድን ናችው?

በቤተሰብ የደም ግፊት ከነበረ በእናት ወይም በእህት
በልጅነት እድሜ የተከሰተ እርግዝና ከ 20 አመት በታች
እድሜ ገፍቶ የተከሰተ እርግዝና ከ 40 አመት በላይ
ባለቤቷን ከቀየረች ይህም ማለት በፊት ሌላ ባል ኖሯት አሁን ደግሞ አዲስ ባል ካገባች በተለይ አሁን ያገባችው ባለቤቷ በፊት የነበረው ሚስት እርግዝና ላይ ግፊት ኖሯት ከነበረ
ከእርግዝና በፊት ግፊት ከነበረ
በበፊት እርግዝና ግፊት ከነበረ
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት
ሌሎች የስኳር እና የኩላሊት ህመሞች ከመፀነሷ በፊት ከነበረ
መንታ እና ከዛ በላይ እርግዝና ካለት ተጠቃሽ ናቸው።

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት መጨመር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት, ይህም በራስ ምታት መድሀኒት የማይመለስ እና የማይቆራረጥ
አይን ብዥ ማለት፣ መጨለም
ጨጓራ በሚያመን ቦታ እና በላይኛው ቀኝ የሆዳችን ክፍል ከፍተኛ የሆነ ህመም
የሰውነት ማበጥ በተለይ በፊታችንና በአይናችን ዙሪያ ፣ ሆዳችን እና እግራችን
በላብራቶሪ የሚታዩ የላብራቶሪ ችግሮች በተለይ የደም ውጤት ላይ፣ የጉበት ምርመራዎች ላይ፣ እና የኩላሊት ምርመራዎች ላይ መጨመር ካለ
የሽንት መጠን መቀነስ ካለ እና ላብራቶሪ ላይ የኘሮቲን መጠን ከጨመረ
ከላይ ላሉት ስሜቶች የህክምና እርዳታ ካላገኘሽ
እራስን መሳት
አረፋን መድፈቅ ፣ ማንቀጥቀጥ
እስከ ህይወት ህልፈት

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ግፊትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቅድመ ወሊድ ክትትል:- ይህም ግፊቱን በቶሎ እንዲገኝ እና መድሀኒትም ካስፈለገ ለመጀመር፣ ክትትልም መጨመር ካስፈለገ እንዲጨመር፣ ሀኪም ቤትም ገብተሽ ተኝተሽ መታከም ካስፈለገሽ ለመወሰን ይረዳል።

የበፊት እርግዝናሽ ላይ ግፊት ተከስቶ ከነበረ እና በዚህኛው ላይ ግፊቱ ከፍተኛ እንዳይሆን ወይም ቀድሞ ከዘጠኝ ወር በፊት በመምጣት ፅንሱ ላይ እና እናትየው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ገና ከ3 እስከ 4 ወር አካባቢ ሊጀመርልሽ የሚችል መድሀኒት ይኖራል።

ከላይ የተዘረዘሩትን የግፊቱን ምልክቶች በማስተዋል እና ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ችግሩ ወደ ከፋተኛ ደረጃ ደርሶ እናትም ላይ ፅንሱም ላይ ችግር ሳያደርስ ቶሎ መከላከል ይቻላል።

ህክምናው

ህክምናው የሚሆነው እንደተከሰተው የእርግዝና ላይ ያለ የግፊት አይነት ሲሆን፤

ከዘጠኝ ወር በፊት ከሆነ እንደየ ግፊቱ አይነት በጣም አጭር የቅድመ ወሊድ ክትትል ቀጠሮዎችን በመስጠት እና ለደም ግፊት የሚሆኑ መድሀኒቶችን በመስጠት ወይም ደግሞ ሆስፒታል በመግባት አልጋ ይዘሽ ፅኑ የሆነ ክትትል ላንቺም ለፅንሱም እየተደረገ ህክምናው ሊሰጥሽ ይችላል።

ሀኪምሽ ከፍተኛ የግፊት ደረጃ ላይ ከሆንሽ እና ከላይ የተጠቀሱት የግፊት ምልክቶች ካሉሽ በመድሀኒት ግፊትሽን በማስተካከል ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ባንቺ ላይ( ደም መፍሰስ፣ ማንቀጥቀጥ፣ እራስ መሳት እና ሞት ሳይከሰት) በፅንሱም( ውሀው ማነስ፣ ፅንስ መቀንጨር፣ ህይወት ማለፍ) ሳይኖር መቆጣጠር ይቻላል።

ሀኪምሽ አሁንም እርግዝናው ላይ እንደተከሰተው የግፊት አይነት በመለየት ፣ እንዳሳየሽው የግፊት ምልክት እና የላቦራቶሪ ውጤቶች መሰረት መቼ እንደምትወልጂ ይወስናል።

አስተውይ:- ይህ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ግፊት እድሜ ሲገፋ ከሚከሰተው ግፊት በዋነኝነት የሚለየው ግፊቱ የሚገናኘው ከእንግዴ ልጁ ጋር ስለሆነ ነው። ስለዚህ ግፊቱ የሚጠፋው ልጁ ሲወለድ እና እንግዴ ልጁ ሲወጣ ብቻ ነው!

ለተከታታይ የጤና ነክ መረጃዎች
https://t.me/Doctormhomecare