Get Mystery Box with random crypto!

☞ ሱባዔ ምንድ ነው አንብቡት አጭር ነው በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አም | አድኅነነ እግዚኦ እስመ ሃልቀ ሔር

ሱባዔ ምንድ ነው

አንብቡት አጭር ነው

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሱባኤ በሰዋሰው ትርጉሙ "ሰባት"ማለት ሲሆን በመንፈስ አተረጋጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከ ዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪየ ጋር እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው ፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ፦ ፈጣሪ አለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፋጥረትን ከመፋጠር ማረፋ ፥ለጸሎት የሚተጉ ምዕመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥር ፋጹምነት ያመለክታል ፡፡ [ዘፍ 2*2 , መዝ 118*164 ] አንድ ሰው 7 ቀናት ቢጾም "አንድ ሱባኤ ጾመ" ይባላል ፡፡

☞ ሱባኤ መቼ ተጀመረ?

የተጀመረው ከውድቀት በሓላ በመጀመርያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያናችን መዛግብት ያስረዳሉ በምላሹም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስጋን ለብሼ ከ 5 ቀን ተኩል በኋላ አድንሃለሁ የሚለውን ቃል ኪዳን የሰማው ሱባኤ በመግባቱ ነው፡

https://t.me/dnhayilemikael

☞ ሱባኤ ለምን ?

የሰው ልጅ ሓጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል ፡፡ በፈፀመው በደል ኀሊናው ይወቅሰዋል ይጸጸታል ፡፡በመጀመርያ ደፋሮ በሰራው ሀጥያት በኋላ ይደነግጣል ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፋጥረት ኀሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው ፡፡ በዚህ ግዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኝት ያስባል ይተክዛል፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ አለም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይህውም በጥቂት ድካም ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባኤ ነው፡፡

➊ እግዚአብሔርን ለመማጸን

ማንኛውም ሰው ሱባኤ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል ፡፡ ምንም የምንጠይቀው ( የምንማፀነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኝው መልስ አይኖርም ፡፡ ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት ፦ሱባዔ የምንገባው ለምንድን ነው ? በማለት እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ፡፡

➋ የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባኤ የቅዱሳን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ በጾመ ነብያት የነብያትን ፤ በጾመ ሀዋርያት የሀዋርያትን ፤በጾመ ፋልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፋ ሱባኤ መግባት የነበረ ነው፡፡

☞ የሱባኤ አይነቶች

1 የግል ሱባኤ ( ዝግ ሱባኤ) ፦ አንድ ሰው ብቻውን አመች ቦታ ማንም ሳያየው በግሉ የጸሎት በአቱን ዘግቶ በሰቂለ ኀሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው በኀቡዕ የሚፈፅመው ሱባኤ ነው ፡፡
2 ,የማህበር ሱባኤ ፦ ካህናት ምዕመናን ወንዶች ሴቶች ሽማግሌወች ፤ወጣቶች ፤በአንድ ሆነው በቤተ ክርስትያንና አመች በሆኑ ቦታወች ሁሉ ተሰብስበው የሚገብት ሱባዔ ነው፡፡
3 , የአዋጅ ሱባዔ ፦ በሀገር ላይ ድንገተኛ አደጋ ፤ አባር ቸነፈር ጦርነት ሲነሳ እንዲሁም በማህበረ ምዕመናን ላይ አስጊ የሆነ መቅሰፋት ሲከሰት እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ አይነት ነው፡፡


☞ቅድመ ዝግጅት
ሱባኤ ከመግባታችንም ሆነ ከገባን ግዜ እንዲሁም ከጨረስን በኋላ ምእመናን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል ፡፡

➊ ሱባኤከመግባት አስቀድሞ

፩ በመጀመርያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡
፪ ሱባኤ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሃ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
፫ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል ፡፡ሱባኤ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡
፬ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡በቤተ ክርስቲያናችን በአብዛሀኛው ግዜ ሱባኤ የሚገባው በአጽዋማት ወቅት በመሆኑ ይህንን መለየት ነው ፡፡ምክንያቱም በጾም ወቅት ብዙ አባቶች ጸሎት የሚይዙበት ስለሆነ ፀሎታችን ከእነርሱ ጋር አብሮ ያርግልናልና ነው፡፡ እዚህ ላይ በማንኛውም ግዜ ሱባኤ አይያዝም ለማለት አይደለም በማንኛውም ግዜ ፈተና ያጋጠመው ሰው ሱባዔ ሊይዝ ይችላል፡፡

➋ በሱባኤ ግዜ

ሀ. በጸሎት ሰአት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምስራቅ መልሶ መቆም ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰቂለ ህሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡
ለ . በቅደም ተከተል መፀለይ ይገባል በመጀመርያ አአተብ ከሚለው ተጀምሮ አቡነ ዘበሰማያትን ጠቅሶ ጸሎተ ሀይማኖትን መጨረስ ፡፡ሰግዱ እና ስለ መስቀል በሚያነሳው ላይ እየሰገዱና እያማተቡ መጸለይ ፡፡ በማስቀጠል አቡነ ዘበሰማያት ፤መዝሙረ ዳዊት ውዳሴ ማርያም ሌሎችንም ማስከተል ከዚያ 41 ግዜ ኪራላይሶ ይባላል ፡፡
ሐ. በሱባዔ ግዜ ከተሐራሚው የሚጠበቀው ነገር ሐጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ለእያንዳንዱ በደል ማልቀስ ማዘን ይገባዋል ፡፡
መ. በመጨረሻም ሱባዔ የገባው ሰው ሱበዔውን ሳይጨርስ ወይም አቋርጦ ከማንኛውም ሰው ጋር ፈፅሞ መገናኝት የለበትም ፡፡

➌ ከሱባዔ በኋላ

ላቀረብነው ተማፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል ፡፡ "ሱባዔ" የገባ ሰው ሁሉ ራዕይ ላያይ ይችላል፡፡ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም ፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኝው የህሊና ሰላም ነው ፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው ፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባኤ ገብተን ያሰብነውን ካላገኝን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት በመማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክብር አሜን ይቆየን


ተቀላቀሉ ቴሌግራም
https://t.me/dnhayilemikael