Get Mystery Box with random crypto!

++እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል+++ {የሳቅ ቅድመ ነገሮች በአሥራው መጻሕፍት} (ሳቅ ጥርጣሬህ | ዲያቆን ሞገስ አብረሃም|moges abreham

++እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል+++
{የሳቅ ቅድመ ነገሮች በአሥራው መጻሕፍት}

(ሳቅ ጥርጣሬህ የሚገለጸበት አንዱ መንገድ ነው......)

በእርጅና ምክንያት ከመውለድ የተገታች ሣራ በእግዚአብሔር ቃል መሳቋን እናስታውሳለን። ነገሩ እንዲህ ነው ከድንኳኑ ደጅ ከአብርሃም ኋላ ቆማ ሳለች እግዚአብሔር እንደ ዛሬ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሳራ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ሲል ሰምታ "ሲያረጁ አምባር ይዋጁ" እንዲሉ እስከዛሬ ድረስ ገና ቆንጆ ነኝን ጌታዬም አርጅቷል ብላ በመጠራጠሯ ብቻዋን ሳቀች። ሳቅ የጥርጣሬ ምልክት መሆኑን በሣራ ታሪክ ውስጥ እንመለከታለን። ጥርጣሬ የሚወልዳቸው እምነት ከመጉደል የሚመጡ ሳቆች አሉ። ካለመኖር ወደመኖር ያመጣ እግዚአብሔርን ተጠራጥሮ መሳቅ ደግሞ ይበልጥ የከፉ ነው። ሳቅህ ጥርጣሬ የወለደው እንይሆን ተጠንቀቅ። ቃል ኪዳን ለተገባለት ለአብረሃም ሚስቱ የምትሆን ሣራ ይህ ሳቋ አስወቅሷታል። ሳራ ለብቻዋ የሳቀችውን ሳቅ እግዚአብሔር በጥበቡ በግልጥ ተመለከተ። ሰውን ተደብቆ ሰው ላይ መሳቅ ይቻል ይሆናል ሰውን ተደብቆ መሸሽ ይቻል ይሆናል ገደል ጠፈር ጣራ ግድግዳ የማይገድበው የእግዚአብሔር ሥራ ላይ ተደብቆ መሳቅና መሸሽ ግን አይቻልም። እግዚአብሔርም አብረሃምን ሳራ ብቻዋን ለምን ተጠራጠረች በውኑ እግዚአብሔር ክረጁ በኋላ እንዲወልዱ ማድረግ እግዚአብሔር ይሳነዋልን። ብሎ ሣራ ለሳቀችበት ጉዳይ መልስ ሰጣት። በተያያዥ መንገድ አለማመንን ተከትሎ የሚመጣ ፌዝ መገለጫ ሳቅ ሊሆን ይችላል። ሳቅህ ጥርጣሬህን ገልጦ እንዳያስወቅስህ ለሚመለከትህ ሰው ደግሞ እያፌዝክበት መሆኑን አስቦ እንዳያዝንብህ ተጠንቀቅ።


(ሳቅ ነቀፌታህና ንቀትህ ሚገለጥበት መንገድ ነው.....)

ቅዱስ ዳዊት “በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።” ይለናል። እግዚአብሔር ይሥቃል? ክብር ይግባውና እርሱ በሰዎች አንጻር እንደምናየው አይነት ሳቅ የሚስቅ አይደለም። ነገር ግን ሳቅ መንቀፍን መናቅን ማቃለልን ይወክላል በሥራቸው ይስቃል ይሳለቅባቸዋል ስንል ሥራቸውን ተመልክቶ ይነቅፉቸዋል ይንቃቸዋል ማለቱ እንደሆነ ልብ በሉ። ስለዚህ በእግዚአብሔር አንጻር ስንመለከተው ተገቢ ሳቅ ነው። በሌላ አገላለጽ በሰዎች ሥራ ማዘንን በራሱ በአግርሞት ሳቅ ሊገለጽ መቻሉ ርግጥ ነው። እግዚአብሔር በሥራችን ቢነቅፈን አምላክነቱ ጌትነቱ ነው። ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ እንዳለው ግን መቆማችን ሳናውቅ በወደቁት የምንስቅ ከሆነ በደል ይሆንብናል። ስለዚህ ሳቅ መናቅን መንቀፍን የሚገልጽ እንቅስቃሴ ነው።

(ሳቅህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ነገር ስትደሰት የምትገልጥበት መንገድ ነው .......)

አስቀድማ ተጠራጥራ የሳቀችው ሣራ “እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል።" ሳራ ካረጀች ሙቀት ልመላሜ ከተለያት በኋላ በመወለዷ መደሰቷን ሳቅ አደረጎልኛል ብላ ተናገረች። ይህንን የመወለዷን ነገር የሰሙ ዘመዶቿ ሁሉ ስለ እርሷ እንደተደሰቱ ለመግለጽ ደግሞ ሰው ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች። በስተርጅና የወለዱትን ልጅ ስሙን "ይስሐቅ" አሉት ይህም "ትፍስሕት" ደስታ ማለት ነው ቀድማ ትወልጂያለሽ ሲላት ተጠራጥራ የሳቀችው ሳራ ዳግመኛ አምና በወለደችው ልጅ የደስታ ሳቅ ሳቀች። በሷ ሳቅም ያያት ሁሉ ሳቅ። ተመልከቱ ደስታ ፊትን ያበራል በእኛ የደስታ ሳቅ ውስጥ ደስ ምናሰኛቸው ሰዎች አሉ። በጥቅሉ ሳቅ የሆናትን ልጅ እግዚአብሔር ሰጣት። እግዚአብሔር ባደረገልን ነገር ስንስቅ ደስታችን እንገልጻለን።

(ቢሆንም ግን ከሳቅ ለቀሶ ከደስታ ሀዘን ሳይሻል አይቀርም........)

ያዕቆብ "ወላሕዉ ወብክዮ" እዘኑ አልቅሱ ይላል። ሳቃችሁን ወደ ለቅሶ ደስታችሁንም ወደ ኃዘን መልሱት ማለት ነው። ተድላ ደስታን ትቶ ማልቀስ አንዱ የጽድቅ መንገድ ነው። በተለይ የጥበብ መጻሕፍት በተደጋጋሚ ያነሳሱታል። ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን እንዲህ ብሎ ገልጾታል "ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።" ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሀዘን ቀድሞ ሲመጣ በፍጻሜው ሳቅ እንደሚሆን ይነግረናል "ብፁዓን እለ ትበክዩ ይእዜ እስመ ትስሕቁ።" ዛሬ የምታለቅሱ የተመሰገናችሁ ናችሁ ትስቃላችሁ ደስ ይላቹሀል። ይለናል። ሀዘን ይዞት የሚመጣ ሳቅ አለ ይህ ፍጹም ደስታ ያለበት ሳቅ ነው።

"በወንድሙ መሳቅ ለሚወድ ሰው ወዳጅ አትሁን" ማር ይስሐቅ

ዲ/ን ሞገስ አብረሃም
23/10/2014