Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ የነሐሴ ፯ ዝክ | ቀሲስ መልአኩ ይፍሩ ዘውሉደ ብርሃን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በዲያቆን መልአኩ ይፍሩ

የነሐሴ ፯ ዝክረ ቅዱሳን።

እንኳን ለዓለሙ ብርሃን እናት #ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_የጽንሰት ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

¶ አመ ፯ ለነሐሴ በዛቲ እለት፥ ፈነዎ እግዚአብሔር ለገብርኤል ሊቀ መላእክት ኀበ ክቡር ወልዑል ኢያቄም ጻድቅ፣ ወአይድዖ በራእይ #ፅንሰታ_ወልደታ_ለእግዝእትነ_ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ወከመ ይከውን ባቲ ፍሥሓ ወመድኃኒት ለኲሉ ዓለም።

፩-ነሐሴ ፯ በዚህች ዕለት እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው፤ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን #ፅንሰቷንና_ልደቷን በርሷም ለዓለሙ ኹሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው።

+ ይህም ቅዱስ ኢያቄም ከሚስቱ ቅድስት ሐና ጋር ልጅ ስላልነበራቸው እጅጉን ያዝኑ ነበር። በዚህም የተነሳ ( አይድሁድ ልጅ የሌለአ ከእግዚአብሔ የተረገመ ጸጋ በረከት የሌለው ነው ብለው ያምኑ ነበርና) ከአይሁድ ብዙ መገለልንና መከራ ተቀበሉ። በዚህም በተለይም ቅድስት ሐና እናታችን ብዙ ታዝን ነበር። አንድ እለትም ቤተ መቅደስ ደርሳ አልቅሳ ስትመለስ ርግቦች ከገላግልቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ አይታ ከእሊህ ግእዛን ከሌላቸው ፍጡራን እኔን የማንስ ድንጋይ ነኝነ ብላ እጅጉን አለቀሰች። እግዚአብሔርም ቸር ነውና ስዕለታቸውን እና ጸሎታቸውን ሰምቶ ራእይን አሳያቸው፣ እርሱ ለርሷ እርሷም ደግሞ ለርሱ።

+ እርሱም ለርሷ ጸዓዳ ዖፍ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በቀኝ ዠሮዋ ገብታ በማኅፀኗ ስታድር፣ እርሷም ደግሞ ኢያቄምን ሲያስታጥቁትና በትሩ ለምልማ አብባ አፍርታ የዓለም ኹሉ ሰው ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከቱ። በዚህም እጅግ በመደነቅ ያለቅሱ ነበር። በጥዋትም ያዩትን ተነጋገሩና ከኹሉ በፊት ጸሎት ያዙበት። ኢያቄምም ለጸሎት ለሱባኤ ወጣ ብሎ ከአንድ ተራራማ ቦታ ገባና በዚያ መትጋት ጀመረ። እነርሱም ኹለታቸው ልጅ ቢሰጣቸው ለእግዚአብሔር እንደሚሰጡ ተስለው ነበርና።

+ በዚህም እለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅዱስ ኢያቄም መጥቶ የምሥራቹን ነገረውና ከቅድስት ሐና እንዲደርስ ይነግረዋል። ቅዱስ ኢያቄምም የእግዚአብሔርን የቸርነቱን ሥራ እያደነቀ ወደቤቱ ተመልሶ በቸሩ አምላክ ቅዱስ ፈቃድ የዓለም ብርሃን የሆነውን እውነተኛ ፀሐይ የወለደችልንን ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና አልባቲ ሙስና የተባለች ወላዲተ አምላክን በዛሬዋ እለት ተፀነሰችልን። ይህንንም ይዞ ታላቁ ሊቅ አባ ሕርያቆስ "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ - ድንግል ሆይ በኃጢአይ በሚደረግ ሩካቤ የተፀነስሽ አይደለም በሕግ በኾነ ቅዱስ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ" ይለናል።

+ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በከበሩ ኢያቄምና ሐና ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

፪-ዳግመኛም በዚህች የሐዋርያት አለቃ #የከበረ_የጴጥሮስ በዓል ነው።

+ በዚህችም እለት ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ቢጠይቃቸው በልባቸው ያለውን ነገር በሌሎች ሰዎች አድርገው ነግረውት ነበር። አስቀድሞም ሐዋርያት (መንፈስ ቅዱስ ገና ስላልተሰጣቸው) ይጠራጠሩ ነበርና ይህነን ነገር ሲጠያየቁ አንዳንዶቹ ኤልያስ ነው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ኤርምያስ ይሆን፣ ሌሎቹም ደግሞ ከነቢያት አንዱ ይሆን? ሲሉ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን እስኪ አቅናለን አንተ ምን ትላለህ ቢሉት፣ ተዉ እርሱስ አምላክ ወልደ አምላክ የኾነ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነው አላቸው።

+ ቸሩ አምላካችንም ይህንን እምነቱን በኹላቸውም ፊት ሊገልጥለት ወደደና በፊልጶስ ቂሣርያ ጠየቃቸው። እነርሳቸውን ያሰቡትን በሌሎች ሰዎች አስመስለው ሲናገሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀበል አድርጎ አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ብሎ መሰከረ። ቸሩ አምላካችንም ይህን ደማዊ ሥጋዊ ዕውቀት አልገለጠልህምና ጴጥሮስ ሆይ አንተ አለት ነህ፣ በአንተም አለትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፣ የሲዖል ደጆችም አይችሏትም፣ ለአንተም የመንግስተ ሰማያትን ቁልፍ እሰጥሃለሁ ብሎታል።

+ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጌቶቻችን በሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለሁላችን ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ዕብል ለጴጥሮስ ሥዩም
ላዕለ ሐዋርያት ኄራን ካህናተ ኲሉ ዓለም
ሶበ ለክርስቶስ አምኖ ከመ ወልደ አምላክ ዮም
ኢከሠተ ለከ ይቤሎ ዘሥጋ ወደም
እንበለ አቡየ ዘሀሎ እምቅድመ ዓለም።

፫-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ጢሞቴዎስ አረፈ።

+ ታላቁ ተጋዳይ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስቆሮስ ካረፈ በኋላ የተሾመ ደገ'ኛ ሊቀ ጳጳስ የነበረ ሲኾን ብዙ መከራን የተቀበለና ገድለኛ አባት ነው። ደጋግመው ከመንበሩ አሳደውት ነበረ፣ መርቅያን የተባለው መናፍቅ ንጉሥ በነገሠ ጊዜ በርሱም ላይ መናፍቅ ጳጳስ ሹሞበት ነበር። መርቅያን ሲሞትም ወደ መንበሩ ተመልሷል። ብዙ መከራን ተቀብሏል። በመርቅያን ልጅ በልዮንም ደግሞ መከራ ስደት ደርሶበታል። ኋላ ግን ዘይኑን ሲነግሥ ዳግመኛ ወደ መንበሩ ተመልሷል። ለሃያ ሁለት ዓመታትም በመንበሩ በበጎ አገልግሎት ሲያገለግል ቆይቶ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

ሰላም ለጢሞቴዎስ እንተ ረሰየ ምርዋጾ
ለምሂር ወለገሥጾ
በመሠረተ ወርቅ ወብሩር ነፍሳተ ብዙኃን ሐኒፆ
ወበእንተ ዘኮነ በስደት ቢጾ
እምዕሴተ ዲዮስቆሮስ አብ ዕሴቱ ኢሐጾ።

፬-ዳግመኛም በዚህች ዕለት የራኄል ልጅ #ዮሴፍ (ወልደ ያዕቆብ) ተወልደ። በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

፭-ዳግመኛም በዚህች ዕለት እግዚአብሔርን የሚወዱት ታላቁ #የኢትዮጵያ_ንጉሥ_አፄ_ናዖድ ዕረፍታቸው ነው። እኒህም ንጉሥ እመቤታችንን የስምንተኛውን ሺህ ዘመኑን አታሳዪኝ ውኃውንም አታጠጭኝ እያሉ ይማጸኗት ነበር። ቸሩ አምላክም ልመናቸውን ተቀብሎ በ፲፬፻፺፱ ዓ.ም ነሐሴ ፯ በዚህች ቀን ወደ ሰማያዊት መንግስቱ ጠራቸው። ንጉሥም መፍቀሬ ድንግል የኾኑ ሲሆን ድርሳናትንም የደረሱ ደገ'ኛ ንጉሥ ናቸው። መልክአ ማርያም የሚባል ታላቅ ጥዑም ድርሰትም አላቸው። በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው በእንተ ቅዱስ ኢያቄም ወቅድስት ሐና ወበእንተ እግዝእተ ኲሉ መድኃኒተ ኲሉ ቤዛዊተ ኲሉ ዓለም ድንግል በክልኤ እምከ ወበእንተ ኲሎሙ ቅዱሳን እለኮነ ተዝካረ በዓሎሙ በይእቲ እለት መሐረነ ለነ ለአበስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን።

እግዚኦ ተዘከር ኪዳን ዘወሀብኮሙ ለቅዱሳን አግብርቲከ ወአእማቲከ እለ አስመሩ ኪያከ፣ ወሶበ ተዘከርከ ዘንተ ተዘከር ከመ መሬት ንሕነ አባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ፣ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለቅድስት ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ወለቅድስት ቤተ ክርስቲያን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሳህልከ እግዚኦ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።