Get Mystery Box with random crypto!

ስለሀገር የመኖር ፅናት~እንደ ወታደር ሀገርን መውደድ ስለ ሀገር መሞገት ከማንኛውም ዜጋ የሚ | የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ _ Commandos and Airborne Command

ስለሀገር የመኖር ፅናት~እንደ ወታደር
ሀገርን መውደድ ስለ ሀገር መሞገት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ በጎ እሳቤ ነው። ነገር ግን ሀገርን መውደድና ስለሀገር መኖር ለየቅል የሚሆኑበት እውነታዎችም አሉ።
  
በስመ - ሀገር ወዳድነት ህጸጽ ብቻ እያነፈነፉ፣ የተፈጠሩ ችግሮችን ከሚገባው በላይ እየለጠጡና ከመጠን በላይ እያገዘፉ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ሲያላዝኑ መዋል የሚያስገኘው ጠብ የሚል ነገር የለም።
   
ይህ ሲባል በሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ዝም ይባል፣ አንዳችም የግል አስተያየት አይሰጥ ለማለት ተፈልጎ እንዳልሆነ ልብ ይባል።
    
ሀገር ትውልድ እስከቀጠለ ድረስ እንደየዘመን ሁነቱ ችግሮች አሉ። ነበሩ። ይኖራሉም። ምክንያቱም ፍጹም ትክክል የሆነ ነገር ከሰው የሚጠብቅ ካለ የራሱን ሰዋዊ እውነታ የዘነጋ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።
   
ከፀሐይ በታች ዓለምን በማያቋርጥ ምርምርና ጥናት እየታገዘ በአስገራሚ ፈጠራዎች የሚያስደምም ግኝት እውን እያደረገ የሰው ልጅ ህይወትና ኑሮን ለእስከዛሬው ዓለማዊ ዕውነት ያበቃው የሰው ልጅ ዕውቀት በብዙ ስህተቶች ባለፈ ጉዞ የተገኘ ትሩፋት መሆኑን ማጤን ግድ ይላል።
   
በተለይ...በተለይ እንደኛዋ ኢትዮጵያችን ዓይነት በየዘመናት አንጓ እየተፈጠሩ በመጡ የታሪክ፣ የፖለቲካና መልከ - ብዙ ስብራቶች እያነከሰች ዛሬ ላይ የደረሰች ሀገር ላይ በጥቂት ዓመታት ሆይ ሆይታ ሁሉም ነገር በምናስበው ልክ ትክክል እንዲሆን መጠበቅ የዋህነት ነው የሚሆነው።
  
"እና ምን? " የሚል ጥያቄ አጭሮብን ይሆን ይሆናል። ምላሹ ከተባለ እንደኔ "ሀገርን ከመውደድ እና ስለ ሀገር ከመሞገት ባሻገር፤ ስለሀገር የመኖር ጽናት ይኑረን።" ነው።
 
" እንደ ማን?" ከተባለ ደግሞ "እንደ ወታደር" እላችኋለሁ።
   
የሀገሬ የሀገራችሁ ወታደር አሁን ላይ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ሆነ ሌሎች ውግንና ነጻ ሆኖ፤"ከራስ በፊት ለሀገርና ህዝብ" በሚል መርህ ሁለንተናውን በሙያዊ ዲሲፕሊን ለሀገሩ ፍቅር አውሎ በሳምንት ሰባት ዕለታት በቀንም ሃያአራት ሰዓታት ያለ ዕረፍት እየሰራ ይገኛል።ሲሰራም እስከሚደክመው ሳይሆን እስከሚሞት ድረስ።
   
በነገራችን ላይ የውትድርና ሙያ በራሱ በስብዕናና ዜግነታዊ ዕምነት ላይ የበዙ በረከቶችን ለግሶ፣ በችግሮች ማላዘንን ሳይሆን፤የመፍትሄ አካልነትን፣ በስሜት ከመንተክተክ ይልቅ ስክንነትን፣ ከሆይ ሆይታ ይልቅ አስተዋይነትን፣በትንሽ ነገር ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ጽናትን የሚያላብስ የሞያዎች ሁሉ በኩርና ክቡር ነው።
   
የውትድርና ህይወት በማያቋርጥ የዕውቀት ዑደት ውስጥ ዕለት በዕለት ማለፍም ነው።በዘላቂ ሳይንሳዊ ተጨባጭ ዕውቀትና ጥበባዊ አመራር እየተገነባ የሚራመድ ተቋም አባል የመሆንን ወርቃማ ዕድል የሚያጎናፅፍም ነውና፤አያልቄ ገጸ - በረከት የሚገኝበትም ነው።
   
ለዚያም ነው  ወታደር በጠባብ ደረቱ በምትገኝ ልቡ ውስጥ ታላቋንና ግዙፏን ኢትዮጵያ ይዟት ለጸና ሰላሟ ሲያካልላት የሚኖረው።
   
በሀገሩ ምንም ቢፈጠር ምን፤ መፍትሄ እንደሚኖር ተስፋ አድርጎ ብቻ ሳይሆን አምኖም ጭምር ስለሰላም ይሰራል።በመስዋዕትነት ታጅቦ።
   
ታዲያ ስለድካሙና ቃላት ሊገልጹት አቅም በሚያንሳቸው ብርቱ ልፋትና ድካሙ ምትክ ክፍያ አይሻም።ክፍያው የሀገሩ መጽናት መከበርና የታላቅነት ጉዞ መቀጠል ነው።
   
እናም ወታደር ሀገሩን ከመውደድ ተሻግሮ ስለሀገር ይኖራል። በታመነና ከእውነተኛ ልባዊ ፍቅሩ በመነጨ ኢትዮጵያዊ እምነት።
   
ይህንን ጽኑ እምነት አይተን፣ ሀገራዊ ችግሮችን ለግላዊ ጥቅም የሚያውሉ ቀላማጅ ዩቱዩበሮች 'እውን የሀገር ተቆርቋሪ ናቸውን?' ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።
   
አንድ ነገር ግን ማለት ግድ ይላል። ሁሉም ዜጋ ባለው ሙያ፣ ዕውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት እንደ ወታደሩ ሁሉ፤ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትቶ፤ የበኩሉን ዜግነታዊ አበርክቶ ለሀገር በመኖር መርህ ቢወጣ ምን ውጤት እንደሚገኝ ለመገመት አይከብድም።
  
እንዲህ ያሉ ዜጎች የሉም ማለት ሳይሆን እልፍ አዕላፍ ቢሆኑ አስባችሁታል?
ክብር ስለሀገሩ በፅናት ለሚኖረው ወታደር

ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

https://t.me/CommandoAndAirborneCommand

YouTube