Get Mystery Box with random crypto!

2ኛ ጴጥሮስ 3 ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯ ¹-² ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ | ኢየሱስ ያለው ህይወት አለው!!!!

2ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ።

³ በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤

⁴ እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።

⁵ ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤

⁶ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤

⁷ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።

⁸ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

⁹ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።

¹⁰ የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።

¹¹-¹² ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤

¹³ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።

¹⁴ ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥

¹⁵ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።

¹⁶ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

¹⁷ እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤

¹⁸ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።



Join us
@Christianslike