Get Mystery Box with random crypto!

*ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ••••••••••••••••••••••••••••••••• “ | ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA

*ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ
•••••••••••••••••••••••••••••••••
“ የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።”
ዘኍልቁ 23፥10
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
የስሙ ትርጉም - በግሪክ ቋንቋ አክሊል ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡

አባቱ ስምኦን፣ እናቱ ሃና ይባላሉ፡፡

የተወለደው - ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ በብፅዓት /በስለት/ ነው፡፡ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለ ቦት ተወለደ ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡

ጥቅምት 17 ቀን ሐዋርያት ሊቀ-ዲያቆናት አድርገው ሾሙት፡፡

ወንጌልን በማስተማሩ አይሁድ በጠላልትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም. በድንጋይ ተወግሮ በስማዕትነት አረፈ፡፡ በዚህም ቀዳሚ-ሰማዕት ተሰኘ፡፡

"ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ፤ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ"

ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁ.6

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በተከራከሩት ጊዜ በመንፈስና በጥበብ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም ዳኞች በተሰየሙበት ሸንጎ ፊት አቅርበው በሐሰት ከሰሱት፤ ሸንጎውም በድንጋይ እንዲወገር ፈረደበት፡፡ እስጢፋኖስ ግን በታላቅ ኃይልና በብዙ መረዳት ከአባቶቻቸው ታሪክ ተነሥቶ የዓለም መድኃኒት የሆነውን ክርስቶስን ሰበከላቸው፡፡ ጥላውን ከአካሉ ጋር እያጋጠመ ወደ ፍጹማን ጥበብ በጽድቅ ቃል መራቸው፡፡ አይሁድ በጣም ተቆጡ፤ ሁሉም በአንድነት ሆነው በድንጋይ ወገሩት፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰውነቱ ቆስሎና ዝሎ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ የልዑልን ክብር ተመለከተ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ቀኝ ቆሞ አየ፡፡ የሐዋ.ሥራ 7÷55፡፡

ቅዱስ አሰስጢፋኖስ “እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስ) በአባቱ ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አላቸው፡፡ አይሁድ ግን ልበ-ደንዳኖች (የማይራራ ጨካኝ ልብ ያላቸው) ስለሆኑ እስጢፋኖስን ከከተማ ወደ ውጭ አውጥተው ደበደቡት፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰውነቱ ደከመ፤ ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ በደረሰች ጊዜ በሞት ጣር ሆኖ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው፤ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ጸለየ፡፡ ነፍሱንም ለታመነው ፈጣሪ አደራ ሰጥቶ ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ ስለ ቅድስ እስጢፋኖስ እንዲ ብሎ ተቀኝቷል፦

“ሰላም ለእስጢፋኖስ በኲረ ሰማዕታት
ሊቀ ዲያቆናት ዐምደ ሃይማኖት
ቅድስተ ሥላሴ ዘርእየ በዐይኑ
ወልዱ ለአብ እንዘ ይነብር በየማኑ
ተቃውሞቶ መዋግድ ዘስእኑ
ነባቤ ጥበብ በልሳኑ
ጽጉያተ ወጽዱላተ አቅማኀ ቃሉ
ማዕከለ አይሁድ በውስተ ዐውድ ዘኮነ ሰማዕተ ወልድ”፡፡

(የሰማዕታት መዠመሪያ የዲያቆናት አለቃ፣ የሃይማኖት ምሰሶ፤ የተለየች ሦስትነትን በዐይኑ ያየ፤ የአብ የባሕርይ ልጁ በቀኙ ተቀምጦ ያየ፤ መከራከሩን ሸፋጮች አይሁድ ያልቻሉ በአንደበቱ ጥበብን የሚናገር የቃሉ ፍሬዎችም ብርሃናውያትና ያበቡለት፤ በአይሁድ መኻከል በዐደባባይ ውስጥ የወልድ ምስክርን ኾኖ ለተገኘ ለእስጢፋኖስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሶታል።

የሰማዕትነት ሕይወትን በመጀመሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር መራራ ሞትን በመታገሡ ቀዳሜ ሰማዕት ተብሏል፤ የቤተክርስቲያን የመጀመሪያው ሰማዕት ነውና፡፡

“በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤”
ዕብራውያን 11፥37

ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን!!!
እኛንም በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን !!!
አምላክ ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን
አሜን!
ተጻፈ:- ጥር 1/2015 ዓ/ም

መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
~•••••••~•••••••~•••••~
“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤” ፩ኛ ዮሐንስ ፩፥፩!
••••••••••••••••••
የፌስቡክ ፔጃችንን ይቀላቀሉ ፤ ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, እና Share ያድርጉ :-
~•••••••~•••••••~•••••~
የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/mikiyas.danail
https://www.facebook.com/profile.php?id=100063973695479
https://www.facebook.com/mikiyas24/
የቴሌግራም ቻናል
: https://t.me/brana_Book