Get Mystery Box with random crypto!

*የክርስቶስ የልደት ቀን የመላው የሰው ዘር የልደት ቀን ነው - the nativity of Chris | ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA

*የክርስቶስ የልደት ቀን የመላው የሰው ዘር የልደት ቀን ነው - the nativity of Christ is the birthday of the whole human race*
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°
"ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና"
ሉቃስ ፪፥፲፩
ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል ፤ አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው። ሁለተኛው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው ። (ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ)
"ህፃን ተወለደልን ፣ ወንድ ልጅም ተሰጠን፣ ስሙም ድንቅ መካር ፣ ኃያል አምላክ የሠላም አለቃ የዘላለም አባት ተብሎ ይጠራል።"
ኢሳ ፱÷፮
የጌታችን ልደት የእኛም የክርስቲያኖች ዅሉ ልደት ነው፡፡ ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች (The three Cappadocian Fathers) አንዱ፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ሊቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ይህን ምሥጢር ሲገልጥ ‹‹The nativity of Christ is the birthday of the whole human race – የክርስቶስ ልደት የመላው ሰው የልደት ቀን ነው›› ሲል መስክሯል (Hyman of praise to the mother of God)፡፡
ዓለምን የፈጠረ የሁሉ ማረፊያ ጌታ ፥ ቤት እንደሌለው በጎል (በረት) ተወለደ ።
አረጋዊ መንፈሳዊ
"ዘይስዕሎሙ ለህፃናት ኀደረ ወተገምረ ውስተ ማህፀነ ድንግል። - ህፃናትን በማህፀን የሚፈጥር ጌታ በድንግል ማህፀን አደረ ተወሰነ።" ቅዱስ ያሬድ
ሊቃውንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እና ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ከምሥጢራት ዅሉ በላይ ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ከማድነቅ ሌላ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በመገረም ይህን ጥበብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ኾኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚኾን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፡፡ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)፡፡
የተወለደው ወልደ አብ ወልደ ማርያም፤ የወለደችው ደግሞ ወላዲተ አምላክ። የተወለደው አምላክ ወሰብእ ፤ የወለደችው ፥ ድንግል ወእም ትባላለችና።
"ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ አማኑኤልም ብላ ትጠራዋለች።" ኢሳ ፯÷፲፬
ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በዓለም ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ጨለማ ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ኾነ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አማናዊው ብርሃን ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ‹‹ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኵሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም፤ በጨለማ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው (ኢሳ. ፱፥፪)፡፡
"በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኖአልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ" ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ
እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ።
መልካም የልደት በዓል !!!
አምላክ ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን አሜን!
ተጻፈ:- ታኀሣሥ/28/2015 ዓ/ም
ዋዜማ
መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
~•••••••~•••••••~•••••~
“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤” ፩ኛ ዮሐንስ ፩፥፩!
••••••••••••••••••
የፌስቡክ ፔጃችንን ይቀላቀሉ ፤ ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, እና Share ያድርጉ :-
~•••••••~•••••••~•••••~
የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/mikiyas.danail
https://www.facebook.com/profile.php?id=100063973695479
https://www.facebook.com/mikiyas24/
የቴሌግራም ቻናል
: https://t.me/brana_Book