Get Mystery Box with random crypto!

ዘሪ ሊዘራ ወጣ ማቴ 13፥3 ገበሬ አንተ ፥ ልትዘራ ስትወጣ ወደ መሬት ልጅህ ፥ ወደ እኔ ስት | ዮሴፍ ጌትነት - Yoseph

ዘሪ ሊዘራ ወጣ
ማቴ 13፥3
ገበሬ አንተ ፥ ልትዘራ ስትወጣ
ወደ መሬት ልጅህ ፥ ወደ እኔ ስትመጣ
ይህንን እይልኝ
ይህንን ተረዳልኝ
ሁሉም እንደሚያውቀው ፥ እኔ የምገኘው ...
በሁሉ ማለፊያ ፥ በዓብይ መንገድ ዳር ነው።
በዚያውም ላይ ሌላ ምልክት
በጭንጫ እኔነት፥ እሾህ አሜካላ ፥ በብዙው በቅሎበት
በምድር መካከል ፥ ታገኘዋለህኝ ፥ የእኔን መሬትነት።
ጌታዬ ...!
እሾህ አሜካላ ፥ በእኔ ላይ እያለ ፥ በእኔ እየኖረ
መሬት ልቦናዬ ፥ በረድኤትህ ቅፅር ደግሞም ካልታጠረ
ጭንጫ ልቦናዬ ፥ ካልተስተካከለ
መልካም መሬትነት ፥ በእኔ ዘንድ ከሌለ
ፍሬን እንደማልሰጥ ፥ ልቤ ስለሚያውቀው
ይህንን እላለው ...
እጠይቅሃለሁ ፥ እሞግትሃለው
ፍሬ ማፍራትን የምትሻ ፥ ይችን ጉስቁል መሬት
ከመዝራትህ በፊት ፥ አንተው አስተካክላት ፥ አንተው አበጃጃት
እሾሁን ነቃቅለህ
አሜካላውን አቃጥለህ
በጸጋ ጎብኝተህ ፥ በረድኤትህ አጥረህ
ከመንገድ ዳርነት ፣ በፍፁም ታደጋት
ፍሬን የምትሰጥ ፥ መልካም መሬም አርጋት
በከኃሊነትህ ፥ እንደገና ስራት
በፈጣሪነትህ ፥ እንዳዲስ ፍጠራት
ያኔ ዘር ብትዘራ ፥ ቃልህን ብትወረውር ፥ አስተውላለሁ...
ቃልህን ጸንሸ ፥ የመንፈስን ፍሬ ፥ በእውነት እሰጣለሁ።

ያሊያ ግን ...
ጭንጫነቴን ሳታስወግድ ፥ ቅፅርን በእኔ ሳታኖር
አሜካላንም እሾህን ፥ ከእኔ ሳትነቅል
እንደይጠቅመኝ እያወቅህ ፥ ዘርን አትዝራብኝ
ዘሪን በማድከምና ዘርን በማባከን ፥ አታስፈርድብኝ

ደግሞም እውነቱን ልንገርህ
አቋሜ ይሄውልህ !
መሬት ነህ ብለኸኝ
በክብር ፈጥረኸኝ
በጭንጫነቴ ላይ ፥ ዘር ሲበቅል ዐይቼ
ልቤን ሐሴት ሞልቶት ፥ በጣም ተደስቼ
ወዲያውኑ የሚደርቅ
በእሾህ የሚታነቅ
በወፍ የሚለቀም
ለማንም የማይጠቅም
ሲሆን ስለ ማዬት ፥ ...
ራሴን እየወቀስኩ
ፍፁም እየተከዝኩ
ላም አለኝ በሰማይ ፤ እንደስካሁን ያለ ፥ ሕይወት ከምገፋ
ጌታዬ ሰርዘኝ ፥ ከፍጥረትነት መዝገብ ፥ መሬት ልጅህ ልጥፋ
ዮሴፍ ጌትነት
27/10/13 ዓ.ም