Get Mystery Box with random crypto!

'የሕይዎት' ና 'የስኬት' ትርጉሙ ጠፍቶብናል። የሰው ልጅ የተፈጠረው በዓላማ ነው። ስለዚህም በተ | ዮሴፍ ጌትነት - Yoseph

"የሕይዎት" ና "የስኬት" ትርጉሙ ጠፍቶብናል።

የሰው ልጅ የተፈጠረው በዓላማ ነው። ስለዚህም በተሰጠው የምድር ላይ ቆይታ ለዓላማ ኖሮ በዓላማ ያልፋል።

አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ሳሉ "ገነትን ያበጃጇት" ዘንድ የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው።
ስለዚህም "ስራ" የሰው ልጆች የመኖር ትርጉም የሚገለጥበት ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው ልጆች የተሰጠ ትዕዛዝና መመርያ ነው።

ለሰው ልጅ መስራት ተፈጥሮአዊ ነው። ስለሆነም እየሰራ ደግሞም ለመስራት ይኖራል።
ለሰራው ስራ እንደ ምስጋናና እና እንደ እውቅና መስጫ የሚሆን በረከት ይሰጠዋል። ይህም የስጋ ብሎም የነፍስ በረከት ነው።
"የስጋ" ቢሉ ፥ ለዕለት ጉርስ ለዓመት ልብስ የሚሆን ዋጋ ያገኝበታል።
"ለነፍስ" ቢሉ በስራው ስላሳየው ትጋት ብፁዕ መባልን ገንዘብ ያደርግብታል።
<<ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው።>> እንዲል የወንጌል ቃል።
ከተፈጠረበት ዓላማ አንፃር
<<መኖሬ ለእኔና ለሌሎች ያለው ሚና ፣ ትርጉምና ፋይዳ ምንድን ነው?>> የሚለው ጥያቄ ፥ የዕለት ከዕለት መልስ የሚያሻው የሰው ልጅ የዘወትር ጥያቄ ሊሆን ይገባል።
ይህም በስራ ይገለጣል።
በኦርቶዶክሳዊ እይታ ስንመለከተው ፥ ስራን የምንሰራበት የመጀመርያው መሰረታዊ ዓላማ ዓለምን ማበጃጀት ነው።
ይህም "ዓለም-ስነፍጥረትን" መልክና ውበት እንዲይዝ ማድረግ ፤ "ዓለም-የሰው ልጅ" ያማረና የተወደደ ሕይዎትን እንዲመራ ማስቻል ነው።
አሁን ላይ ሁላችንም የትርጉም ተፋልሶ አጋጥሞናል። ትልቅ ትውልድ ክፍተት /Generation Gap/ ይስተዋላል።
የመስራታችን ዓላማ ፥ ከስራ መሰረታዊ ዓላማ አፈንግጧል።
ሕይዎትን የማበጃጀት ትርጉማችን ተንሽዋሯል።

የእኛና የሌሎችን ሕይዎት የሚያበጃጀው ስራ ሳይሆን ገንዘብ መሆኑን ወድ0 ማመን ደርሰናል።
<<ብዙ ብር የሚያስገኝ ስራ ?>> የእኔና የሌሎችን ሕይዎት የሚያበጃጅ ፥ የማ/ሰብን ችግር የሚቀርፍ ስራ ምንድን ነው ብለን አንጠይቅም። ማሰብም አንፈልግም።

የስኬታችን መመዘኛም ፥ በተሰጠን ዕድሜ ለሌሎች የሰጠነው አገልግሎትና ያበጃጀነው ሕይዎት ሳይሆን ፥ ያገኘነው የቁስና የገንዘብ መጠን ሆኗል።
ስለዚህም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ወይም የሰዎች አገልጋይ ሳይሆን ገንዘብን የምናገለግል ሁነናል።
"የሰው ልጅ ሰውን ሊያገለግል እንጅ እንዲያገለግሉት አልመጣም" ያለንን ጌታ የሚያስመስለንን ስራ ገንዘብ አላደረግንም።

ወንጌል "ሰው ለሁለት ጌታ አይገዛም" ብሎናል። በስራችን የእግዚአብሔርን አሳብ ወይም የሰውን ልጅ ለማገልገል ካልተጋን ፤ ገንዘብን የምናገለግል ስለመሆናችን ለጌታ አልተገዛንም ማለት ነው።
በሁለት ልብ የምናነክስ ሆነናል።
ስለዚህም ደስታ የመንፈስ ፍሬ ነው ። እውነተኛ ደስታን በስራችን ውስጥ ልናገኘው አንችልም።
ብዙ የሰራን ፣ ብዙ የደከምን ቢመስለንም ያገለገልነው ገንዘብን ብሎም የስጋ ፈቃዳችን እንጅ ፥ የእግዚአብርን አሳብ አይደለምና ደስታ ይርቀናል።
እናስተውል ! ራሳችን እንፈትሽ!
• ስንማር ፥ በእኔ ዙርያ ያሉትን ሕይዎት ለማበጃጀት ፣ ችግራቸውን ለመፍታት ልማረው የሚገባኝ እውቀት ፣ ልይዘው የሚገባኝ ጥበብ ምንድን ነው ብለን ዐቅደን እናውቅ ይሆን?
• ያለኝን እውቀትና ጉልበት ተጠቅሜ ልፈታው የምችለው የማ/ሰብ ችግር የትኛው ነው ብለን አስበንስ?
• እየሰራሁት ባለሁት ስራ የተስተካከለ የሌሎች ሕይዎት ፣ የተፈታ ችግር ምንድን ነው? የእኔ ጨውነት ፣ ብርሃንነት ፣ እርሾነት የት አለ?
ብለን ስራችንን መዝነናል?

እንዲያ ቢሆን ኖሮ ...
• ስራችን የማስመሰል አይሆንም ነበር።
• ስራችን አድካሚ ቢሆንም እንኳ ፥ በድካማችን ደስ የሚለን በሆንን የነበር።
• አንዳችን የሌላችን ሕይዎት የምናበጃጅ ስለመሆናችን ፤ በእኛ ዘንድ ፍቅር በዝቶ በተትረፈረፈ የነበር።
•የዕለት ስራችን በረከተ ስጋ ወነፍስ የሚያስገኝልን በሆነልን የነበር።

እንዲያ ግን አልሆነም...
በዙርያችን ያሉትን ሰዎች ችግር ከማየት አንጀምርም ። ጥሩ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች ፥ እየሰሩ ስላሉት ነገር እንጅ።

ከማ/ሰቡ የምናገኘውን ጥቅም እንጅ ፤ ለማ/ሰብ የምናስገኘውን ጥቅም ፥ የምንጨምረውን ፋይዳ የምናመጣውን መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥተን ስራ አንጀምርም።
ስለዚህም ስራችን ሌሎችን ከድካማቸው የሚያሳርፍ አይደለም። ገንዘብ እንጅ ርካታ ከኛ ርቊል። በስራችን የሌሎችን እንባ ለማበስ አልታደልንም።

ነጋዴው ፥ ማ/ሰቡ የጎሰለውና። ያጣው እኔ የምጨምርለት ነገር ምንድን ነው በሚል ስሌት ስራውን አይጀምርም።
የመኪና አሽከርካሪው ፥ የተጓዦችን ችግር መፍታትን ተቀዳሚ ስሌት አያደርግም።
መ/ሩ ፥ የተማሪዎቹን አዕምሮ መቅረፁ ተጨማሪ እንጅ ቀዳሚ ገዳዩ አልሆነም።
ሀኪሙ ፥ የታመመ የሰው ልጅ - በመዳኑ ውስጥ ያለው ሚና ነፍሱን የሚሰጥለት ተቀዳሚ ጉዳይ ሲሆን አይታይም።
መሐንዲሱ ፥ የሚፈታው የመንገድ ፣ የውሃ ፣ የመብራት ፣ ... ችግሮች ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ጉዳዩ ናቸው።
ዳኛው ፥ "ድሃ እንዳይበደል ፣ ፍርድ እንዳይጓደል" የሚል የስራ መርሁን የሚጋርዱበት ፥ ሌሎች ጉዳዮች አሉት።
ባለስልጣኑ ፥ ሌሎችን ሊያገለግልበት የተሰጠውን ስልጣን - ሌሎች እንዲያገለግሉት የመጎሰሚያ በትር ያደርገዋል።
ፖሊሱ ፣ ... ሌላውም ሌላውም
አሁን አሁን ይህ ጉዳይ ወደ ሃይማኖት ተቋማትም ተጋብቷል።
ይህም ለማ/ሰቡ እንድናበረክት ከያዝነው ኃላፊነት /የስራ ድርሻ ይልቅ/ ፥ እሱን ተጠቅመን የምናገኘው ገንዘብ ተቀዳሚ ዓላማ ሆኗል።
ይልቁንም ደክምን ከምናገኘው ገንዘብም ባሻገር የተመደብንበትን የስራ መደብ ተጠቅመን ፥ የሌሎችን የድካም ዋጋ ያላግባብ የምናግበሰብስበትን መዋቅራዊ አሰራር ወደንና ለምደን ተቀብለነዋል።

በአካባቢያችን ነግዶ ያተረፈ ስናይ ፤ ከሱ አጠገብ ተመሳሳይ የንግድ ስራ ይዘን ቁጭ እንላለን። ሌላም ሌላም የዚህ ነፀብራቆች ናቸው።

ያልሰራንበትን ስናገኝ ጥቂት ለአዕምሮአችን አይከብደንም። እጅ ስመን እንቀበላለን።
ለመኖር የምንሰራ እንጅ ፤ ለመስራት የምንኖር አይደለንም።
ስለማይቻል እንጅ ቁጭ ብለን ፥ መብላት ብንችል ኖሮ ወይም ምግብና ልብስ መሰረታዊ ፍላጎቶች ባያስፈልጉን ኖሮ ስራ ለምኔ የምንል ሰዎች በሆን የነበር።
ብቻ ... ስንቱ ...
ምን ይሻላል ትላላችሁ ... ?
20/10/2014 ዓ.ም
ዮሴፍ ጌትነት